Fana: At a Speed of Life!

የሕጻናትን መቀንጨር ለመከላከል የአመጋገብ ሥርዓት ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕጻናትን መቀንጨር ለመከላከል ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአስተሳሰብና የአመጋገብ ሥርዓት ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን በክልሉ የነበረውን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም በተመለከተ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የፕሮግራሙ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት፤ የሕጻናት መቀንጨር እና የእናቶች ሞትን ለመከላከል የፕሮግራሙ አስፈላጊነት ጉልህ ነው።

በመሆኑም ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸው፤ ማኅበረሰቡ ባመረተው ልክ እና ያለውን ፀጋ በመጠቀም ለልጆች የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ መቀንጨርን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ምርታማነትን በማሳደግ ድህነትን መቅረፍ፣ የተሻለ የአመጋገብ ባሕልን በመፍጠር የሕጻናትን የመቀንጨር ችግር በዘላቂነት መፍታት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የመቀንጨር ችግርን የመቀነስ እንቅስቃሴው ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች እና በመንግሥት መዋቅሮች የጋራ ርብርብ ሊተገበር እንሚገባም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሰቆጣ ቃልኪዳን አማካሪ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ሰፊ የማምረት አቅም ቢኖርም ችግሩን በሚፈለገው ልክ የመቀነስ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾኑን መግለፃቸውን አሚኮ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.