Fana: At a Speed of Life!

የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ከድር ጁሃር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

የአስተዳደሩ የሴክተር ተቋማትና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ዘርፎች የዘጠኝ ወራት አፈፃፃም ሪፖርት እየተገመገመ ነው።

በዚህም በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሀብትና በመልካም አስተዳደር የተከናወኑ ስራዎች በትኩረት እየተፈተሹ መሆኑ ታውቋል።

ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አበረታች ለውጦች እያመጡ ናቸው።

በተለይም ስራ አጥነት ችግር ለመፍታት፣ ለነዋሪዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብና የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ለውጦች በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ርብርቡን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በተመሳሳይ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከሉና ከተማዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ የተከናወኑ የማህበራዊ ዘርፍ ተግባራት በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፥ የተጀመሩ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሂደቶችን በማጠናከር የህዝብ ጥያቄዎችን የመመለስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዘንድሮ የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በድሬዳዋ ያካሄዱት ድጋፋዊ የግምገማ ሂደትና የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በላቀ ደረጃ በመፈፀም ድሬዳዋ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ሂደቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በበጀት አመቱ 124 ነባርና አዳዲስ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚያቃልሉ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የፕላንና ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኃይለማርያም ዳዲ ናቸው።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል 12ቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ፤ ሠባቱ ደግሞ በመጠናቀቅ እንደሆኑ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በተከናወኑ ተግባራትም በዘጠኝ ወራት ከ3 ቢሊየን 234 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ በማግኘት የዕቅዱ 85 በመቶ መሳካቱን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.