Fana: At a Speed of Life!

ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን መደገፍ ይገባል አሉ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በጋራ መደገፍ ይገባል ሲሉ የመላው አፋር ህዝብ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ተናገሩ።

የእውቁ ሱልጣን አሊሚራህ ልጅ የሆኑት 15ኛው የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ከውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል።

ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በሰጡት አስተያየትም በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማትና ኢንቨስስትመንት እንቅስቃሴዎችን ከዳር ለማድረስ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል።

ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለሰላም ዘብ እንዲቆሙና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንዲደግፉም ጠይቀዋል።

በአፋር ክልል በሰብል ልማት ረገድ የመጣውን እምርታ ጨምሮ በለውጡ መንግስት በሁሉም መስኮች ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን እያከናወኑ ያሉትን ስራ እንደሚደግፉም ነው የገለጹት፡፡

ከአፍሪካ ነጻነት በኋላም በበርካታ አፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛት ድንበሮች እንዲቀጥሉ መደረጉን አስታውሰው ፥ ይህም ኢትዮጵያን የባህር በር እንዳሳጣት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ቁጥርና እያሰመዘገበች ካለው እድገት አንጻር የባህር በር የመጠቀም ጥያቄዋ ተገቢ መሆኑን አንስተው፤ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንደሚሻም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ በበኩላቸው ÷ሱልጣን አህመድ የመላው የአፋር ህዝብ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በልጅነታቸው ጀምሮ የታገሉለት የአፋርን ህዝብ ነጻነትና ልማት እውን ማድረግ የሚያስችል ስርዓት በመገንባቱም ከመንግስት ጎን ቆመው ትልቅ ቁም ነገር ማከናወናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ÷ ሱልጣኑ ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ የፌዴራልና የክልል መንግስታትን በሰላምና ልማት ስራዎች ሲደግፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ሱልጣን አህመድን ከመሰሉ የህዝብ ባህላዊና ኃይማኖታዊ መሪዎች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.