Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራት ለቅድመ አደጋ መከላከል ስራ የተለየ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአፍሪካ ሀገራት የቅድመ አደጋ መከላከል ላይ አበክረው በመስራት በአደጋ የሚመጣ ጉዳትን መቀነስ እንደሚኖርባቸው የአፍሪካ ሕብረት አሳሰበ።

14ኛው የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ተቋም ስምምነት(ARC Treaty) ፈራሚ ሀገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።

በስብስባው ላይ የተቋሙ አባል ሀገራት አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍል አመራሮች፣ የአፍሪካ ሀገራት የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮችና የዘርፉ ተዋንያን ተካፍለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍል የዘላቂ ከባቢ አየር ዳይሬክተር ሀርሰን ንያምቤ ሀርሰን አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለተለያዩ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጋለጠች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ሕብረቱ የሚደርሱ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከልና የድህረ አደጋ ምላሽ አቅምን ማጎልበት ላይ ከአባል ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የቅድመ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በመገንባት ሀገራት ከማዕከሉ በሚያገኙት የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ድህረ አደጋ ምላሽን መሰረት ያደረገ የመከላከል ስራ ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የአፍሪካ ሀገራት ለቅድመ አደጋ መከላከል ስራ የተለየ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ዳይሬክተር ጀነራል ኢብራሂማ ቼክ ዲዮንግ ተቋሙ የአፍሪካ ሕብረት ካስቀመጣቸው ስትራቴጂዎችና ግቦች ጋር የተጣጣመ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ሀገራት ለአደጋ ስጋት አስተዳደር የሚመድቡትን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሀገራቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ዙሪያ ያላቸውን ተሞክሮ መለዋወጥና በትብብር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የተቋሙ አባል ሀገር በመሆንና የማቋቋሚያ ስምምነት በመፈረምና በማጽደቅ ተሳትፏቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በስብሰባው ሌሴቶ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ቢሮ ሊቀ መንበርነትን ከሶማሊያ የተረከበች ሲሆን÷ ሊቀ መንበርነቷ ለአንድ ዓመት ይቆያል።

የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ እ.አ.አ በ2012 የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 39 አባል ሀገራት አሉት።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.