Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ በ25 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የ15 መንገዶች ግንባታ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  ከ25 ነጥብ 8ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት 15 መንገዶችን ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር ስምምነት  ተፈራረመ።

መንገዶቹ  አንድ ሺ ሀያ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሲሆኑ÷ አንድ ከባድ የመንገድ ጥገናና አንድ የጠጠር መንገድን ጨምሮ ቀሪዎቹ በአስፋልት ደረጃ የሚገነቡ ናቸው ተብሏል።

መንገዶቹን ሰርቶ ለማጠናቀቅም እንደየ መንገዱ ሁኔታ  ከአንድ አመት እስከ አራት አመት ጊዜን የሚወስዱ መሆናቸው ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት÷ ከፍተኛ ህዝባዊ ጥያቄ ይነሳባቸው ከነበሩትን መንገዶች መካከል ወደ ግንባታ ለመሸጋገር በመብቃታቸው ለአገራችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያበረክቱ ት አስተዋፅዖ ከፍ ያለ  ነው ብለዋል።

ቀደም ብለው ከተፈረሙ መንገዶች መካካል በውላቸው መሰረት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ 20ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲሸጋገሩ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

አያይዘውም 21የመንገድ ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን÷ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የሚገኙ 15ፕሮጀክቶች ወደ ፍጻሜቸው እየተቃረቡ መሆናቸውን ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

የእነዚህ 15 መንገዶች ግንባታ ወጪም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን ፕሮጀክቱን ከፈረሙ 11ተቋራጮች መካከልም 7ቱ ሀገር በቀል ተቋራጮች  ናቸውም ነው የተባለው ።

መንገዶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙና በጠጠር ደረጃ የነበሩ ከመሆናቸውም ባለፈ ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች ምቹ ያልነበሩና ለዘመናትም የህዝብ ጥያቄ ሆነው የቆዩ መሆናቸው ተነግሯል ።

በጥቅሉ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ የጎን ስፋት በገጠር 10 ሜትር ሲሆኑ በዞን ፣ በቀበሌ ፣በወረዳ ፣እና በዞን እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ስፋት ይኖራቸዋል ተብሏል።

መንገዱ ሲጠናቀቅም በአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮና ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ የተገለፀ ሲሆን ÷እንደ ሀገርም የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

በትዝታ ደሳለኝ

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.