Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልምድ በመውሰድ እንሠራለን- ኡጋንዳ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልምዶችን በመውሰድ የሀገራቸውን አየር መንገድ ለማሳደግ እንደሚሠሩ የኡጋናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናኽ ናባኒያ ገለጹ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ ዴንጌ ቦሩ በኡጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተመራ ልዑክ ጋር በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ የኢትዮጵያን የምድር ባቡር ታሪክ አሁን እስከደረሰበት የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማኅበር ድረስ ያለውን የምድር ባቡር አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታው አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ሂደት ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን በባቡር መሰረተ-ልማት፣ በመንገድ፣ በአውሮፕላን ማረፊያ መሰረተ-ልማት ግንባታ እና በሕዝብ ትራንስፖርት የ30 ዓመት መሪ ዕቀድ አዘጋጅታ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ በአፍሪካ ረጅም ታሪክና አኩሪ አፈፃፀም ያለው መሆኑን ጠቅሰው÷ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ መዳረሻዎች በትጋት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናኽ ናባኒያ በበኩለቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ኩራት መሆኑን ገልጸው ከተቋሙ ልምድ በመውሰድ የኡጋንዳ አየር መንገድን ለማሳደግ እንደሚሠሩ መናገራቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በመንገድ መሰረተ-ልማት እና በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለውን ልምድ በመለዋወጥ እድገት ለማምጣት እንጥራለን ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.