Fana: At a Speed of Life!

በአንዲት ሴት ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በሁሉም ሴቶች ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ማመን አለብን- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአንዲት ሴት ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በሁሉም ሴቶች ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ማመን አለብን አሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ በዛሬው እለት መልእክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመልእክታቸው፥ በቅርቡ የተሰማው አሳዛኝ ዜና ኮሮና ቫይረስ በአገራችን ከተከሰተ ወዲህ አንድ መቶ አንድ ሴቶች፣ ሴት እና ወንድ ሕፃናቶች ሳይቀሩ መደፈራቸውን ነው፤ ይህ አስደንጋጭ ዜና ነው ብለዋል።

በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለውና ከባህላችንና ከእምነቶቻችን የራቀ ተግባር ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ የተጎዱት ሴቶች እና ሴትና ወንድ ህጻናት ፍትህ ማግኘት አለባቸው ሲሉም ገልፀዋል።

ሳንዘናጋ፤ በአግባቡ ተቀናጅተን በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ለሃገር ጠንቅ ስለሆነ እንደዋንኛ የጋራ ጠላት ልንዋጋው ይገባናልም ብለዋል ፕሬዚዳንቷ በመልእክታቸው።

ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ባለፈው እሁድ ጠዋት በአዲስ አበባ የሚገኘውን ጊዜያዊ የሴቶች ማረፊያ ማዕከልን የመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር፡፡ በዚህ መጠለያ የሚገኙ ሴቶችና ሴት ህፃናት የሚደርስባቸው ተገዶ መደፈር የሚያስከትለውን ሰቆቃ መቀበል ሲያቅታቸው ጠፍተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄዱ ናቸው፡፡ ወደ ነባር መጠለያ ቤቶች ከመላካቸው በፊት ከኮሮና ቫይረስ ነጻ መሆናቸው እስከሚረጋገጥ በጊዜያዊነት በዚህ ስፍራ ቢበዛ ለአንድ ወር የሚቆዩ ናቸው፡፡

በዚህ ማረፊያ ቤት በነበረኝ ጉብኝት እጅግ የሚዘገንንና ልብ የሚሰብር የሰቆቃ ታሪካቸውን አጫውተውኛል፡፡ ባይናገሩ እንኳን ያለፉበትን መከራና ስቃይ ከአይኖቻቸው፣ ከሁኔታቸውና ከአለባበሳቸው እንደ መጽሐፍ ይነበባል፡፡

በኢትዮጵያ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸመውን የጥቃት ዓይነት፣ ስፋት፣ ጥልቀት፣ ባህሪና ስልት ምን ያህል ውስብስብና ለመቀበል ከአዕምሮ ያለፈ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ለምሳሌ፡-

  • በወላጅ አባቷ በተደጋጋሚ የተደፈረችና ሌሎች እህቶቿ ላይ ተመሳሳይ በደል እንዳይደርስ በማለት ደፍራ ያመለጠችው የአካል ጉዳተኛ፣
  • በ13 ዓመቷ በገዛ ወንድሟ የተደፈረች እህት፣
  • በ13 ዓመቷ ትምህርት ቤት ያልገባችውና በጎረቤት በአሰቃቂ ሁኔታ የተደፈረች ጨቅላ፣
  • ሥራ እናስገባችኋለን በሚል ማታለያ ወጣትነታቸውንና የዋህነታቸውን ተጠቅመው በደላሎች የተደፈሩና
  • የራሳቸውን ልጅነት ሳይጨርሱ ልጆች የወለዱ ወገኖቼን አሳዛኝ ታሪክ አዳምጫለሁ፡፡

የሠማሁት ሁሉ አንድ ህሊና ያለው ሰው ይህን ተግባር ይፈጽማል ብሎ ለማሰብ የሚከብድ ልብን የሚሰብር እና አጥንትን ሠርስሮ የሚገባ ትዕይንት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰቆቃው መቼ በዚህ ያበቃና!

ሌላዋ ለጋ ወጣት ደግሞ የሚከተለውን እንባዋ እንደ ጎርፍ እየወረደ አወጋችኝ፡፡ በአንድ ግለሰብ ተታላ ካረገዘች በኋላ በተፈጠረው እርግዝና ምክንያት ከቤት ሠራተኛነት በተደጋጋሚ ስትባረር ቤተክርስቲያን ማደር የህይወቷ አይቀሬ ዕጣ ፈንታ ሆነ፡፡ ይህንን ጉዳይ ያስተዋለች አንዲት ሴት ወጣትዋ መንታ ልጆችን እንድትገላገል ረዳቻት፡፡

ከማረፊያ ቤቱ ሠራተኞች የሰማሁት ሌላው አሳዛኝ ታሪክ ከሁሉ በላይ ለመስማትም ሆነ ለማውራት የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ አደንዛዥ እፅ በመስጠት በተደጋጋሚ ከደፈራት አባቷ አርግዛ የተገላገለችው ሴት ያለችበትን የመንፈስና የአዕምሮ ስብራት ማን ይጠግናት ይሆን? ያለችበትን ውጥንቅጥ ለማሰብም ሆነ ለመገመት ያዳግታል፡፡ ይህች ወጣት የሥነ ልቦና ህክምና ድጋፍ እያገኘት በመሆኑ በአካል አላገኘኋትም፡፡ ልጇም ለህፃናት ማሳደጊያ ተሰጥቷል፡፡

እነዚህ ገና የልጅነት ዕድሜያቸውን ያልጨረሱ እና በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት የነበረባቸው ሴት ልጆች ተደፍረው፣ ከቤተሰብም ሆነ ከሕብረተሰቡ ሊደርስባቸው የሚችለውን መገለል ሰብረው ወደ ፖሊስ ለመምጣት ያሳዩት ከፍተኛ ድፍረት በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡

እነሱን ሳነጋግር ሳለሁ ወደ አዕምሮዬ የመጣው ነገር ይሄኔ በየቤቱ የሚደርስባቸውን በደል ማንም ሳያውቅላቸውና ማንም ሳይሰማቸው፣ ሳያምናቸው በስቃይ ላይ እስከወዲያኛው ያሸለቡት ናቸው፡፡ ቤት ይቁጠራቸው፡፡

የዚህ ማረፊያ ማዕከል መከፈት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የእነዚህ ጥቂት መጠለያዎች መኖር የፖሊስን ሥራ የሚያግዝ ቢሆንም ሴቶቹ ወደ ፍትህ የሚመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ብሎም ፍትህ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

የተደረገው ጥረትና ርብርብ በጣም ያስመሰግናል፡፡ ሠራተኞቹም የሚደነቁ ናቸው፡፡ ለዚህ የተባበሩ መንግሥታዊና የውጭ ድርጅቶችም ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ይሁንና ሴቶች ልጆችን ከፖሊስ ተረክቦ እንደዚህ ዓይነት እንክብካቤ በመስጠት ለማረጋጋት፣ ለማከም፣ ከደረሰባቸውም ሰቆቃ ለማገገም እጅግ በጣም የረዳ ቢሆንም አገልግሎቱ ጊዜያዊ ብቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ቋሚ መጠለያዎች በጣም ጥቂት በመሆናቸው እንኳን ተጨማሪ ሊቀበሉ ይቅርና በዚህ መጠለያ ያሉትንም በአግባቡ ለማገልገል አስቸጋሪ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ችግሩን ከሥሩ ለመንቀል የሚከተሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡

1ኛ. ይህን አስከፊ ወንጀል የፈጸሙትን ወንጀለኞች ለፍርድ አቅርቦ ተመጣጣኝና አስተማሪ የሆነ ቅጣት ካልተሰጠ በስተቀር ይህ እኩይ ተግባር ይቆማል ብሎ መገመት ዘበት ነው፡፡ ስለዚህም ዘላቂ መፍትሔ ካልተገኘ ሥር የሰደደውን ችግር ሳይሆን ምልክቶቹን ማከም ይሆናል፡፡

2ኛ. ትክክለኛውን መረጃ ከትክክለኛው ምንጭ በቀላሉ የሚያገኝበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡ ለምሳሌ፡-

ተጎጂ ሴቶች «ፍርድ ቤቶች ዝግ ስለሆኑ» ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ነግረውኛል፡፡ ይህም የሆነው ትክክለኛ መረጃ ስለሌላቸው ነው፡፡ በተደጋጋሚ በቅርብ ሰው የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ስለዚህም ከነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች ጋር በጥምረት የሚሰራ የመረጃ አቅርቦት፣ የህግ ድጋፍ እና የመሳሰሉ አገልግሎቶን የሚሰጡ አካላት ያስፈልጋሉ፡፡ ካሉም መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

3ኛ. ሴቶችና ሴቶች ልጆች በዚህ መጠለያ አስፈላጊውን ጊዜያዊ ከለላ ካገኙ በኋላ ረጅሙን የሕይወት ጉዞ ለመጋፈጥ መማር፣ ሙያዊ ስልጠና ማግኘት፣ ሥራ መሥራት፣ አምራች ዜጋ መሆንና የራሳቸውንም ቤተሰብ ወደ መመስረት ካልተሸጋገሩ አሁን የምናደርገው ጥረት ከጊዜያዊ መፍተሔነት ያለፈ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የተቀናጀነና ሙሉ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከዚህ ያለፈ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ተቀናጅቶ መሥራትን ባህል ማድረግ አለብን፡፡

4ኛ. ሕጎቻችን የተበደሉ ሴቶችን ምን ያህል በአግባቡ የሚደግፉ መሆናቸውን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመነሻውም ጾታዊ ጥቃት ተገቢውን ትርጓሜ ይዞ ተገቢው ቅጣት ሊኖረው ይገባል፡፡

5ኛ. ስለሴቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ሥር የሰደደ የተዛባና አድሎአዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ሊለወጥ ይገባል፡፡

ማህበረሰባችን የሚፈጸመውን አስገድዶ መድፈር ያለ እድሜ ጋብቻን፣ ሴትን ልጅ ዝቅ አድርጎ መመልከትን መቃወምና መጠየፍ አለበት፡፡ ለችግሩ ምክንያት በሆኑ በጣም ጥቂት ወንዶች ሳቢያ እጅግ መልካም አርአያና ምሣሌ የሆኑ ብዙሃኑ ወንዶች አባቶች፣ ወንድሞች አሉን፡፡ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ለመልካሞቹ ስንል በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ከፍተት ካልተደፈነ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ አያገኝም ፡፡ ጉዳዩ ከመንግስት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የአጋር ድርጅቶችን ከፍተኛ ቅንጅትንና ትብብርን እንዲሁም አጠቃላይ የማህበረሰቡን ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሚያስመሰግን ሥራ የሠሩ የመጠለያ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ የሴቶች ማህበራት፣ የሴቶች የህግ ባለሙያዎች ፣ የሴቶች ቅንጁት ማህበራት በሥርዓተ ጾታ እኩልነት ዙሪያ የሚሰሩና የሴት መብት ተሟጋቾች አሁንም ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡ ለሚያደርጉት ሁሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ አብረን ነን፡፡

ለመሆኑ ግን ስንቶቻችን ነን የሴቶች መጠለያና ማረፊያ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን የምናውቅ? ተጐጂዎችን የጎበኘን? የረዳን? ስንቶቻችን ነን ሌሎች መጠለያዎች እንዳሉ የምናውቅ? ስንቶቻችንስ ነን ተመሳሳይ ተቋሞች እንዲቋቋሙ የረዳን? ጥቃት ለደረሰባቸው ወንዶች ልጆች መጠለያ መኖሩን የምናውቅ? የጾታ ጥቃት ለሚደርስባቸው በርካታ መጠለያዎች ያስፈልጉናል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይገባናል፡፡

በቅርቡ የተሰማው አሳዛኝ ዜና ኮሮና ቫይረስ በአገራችን ከተከሰተ ወዲህ አንድ መቶ አንድ ሴቶች፣ ሴት እና ወንድ ሕፃናቶች ሳይቀሩ መደፈራቸውን ነው፡፡ አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለውና ከባህላችንና ከእምነቶቻችን የራቀ ተግባር ነው፡፡ የተጎዱት ሴቶች እና ሴትና ወንድ ህጻናት ፍትህ ማግኘት አለባቸው፡፡

ከትምህርት ቤቶች መዘጋት ጋር ተያይዞ ከ30 ሚልዮን በላይ ተማሪዎቻችን ቤት ውለዋል፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ከአንድ ክልል ብቻ 500 ሴት ወጣቶች ያለ ዕድሜያቸው ተድረዋል፡፡ ወደ 1 ሺ የሚጠጉ ጋብቻዎችን ማስቀረት ተችሏል፡፡ በብዙ ጥረት ሴቶች ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ቢደረግም ችግሩ ገና አልተቀረፈም፡፡ ከኮሮና ቫይረስ በኋላ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ በርካታ ሴት ተማሪዎች ላይመለሱ ይችላሉ፣ ግኝቶቻችን ወደ ኋላ እንዳይመለሱ የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡ የወቅቱ ሁኔታ ምን ዓይነት አደጋ ላይ እንዳሉ ያሳየን ከመሆኑም በላይ ት/ቤት ለሴት ተማሪዎች ከብዙ አደጋ መጠበቂያቸው እንደሆነም አረጋግጧል፡፡ ትምህርት ቤት ለሴት ልጆች ያለ ዕድሜ ጋብቻን የሚያስቀርና እና በቤት ውስጥ ካለ ተደራራቢ የሥራ ጫና የሚያሳርፍ መሆኑም ተረጋግጧል፡፡

መዘንጋት የሌለብን ትልቁ ጉዳይ፡- በአንዲት ሴት ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በሁሉም ሴቶች ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ማመን አለብን፡፡

የሚደፈሩ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ስቃይና ሰቆቃ አሳዛኝና መሪር ነው፡፡ የአገር ሀብት በከንቱ እየጠፋና እየባከነ ነው፡፡ ከኮሮና ቫይረሱ ጋር ብቻ አያይዘን እንዳናየው እሠጋለሁ፡፡ ከእርሱ ጋር ለአንድ ወቅት ጮኸን ከወረርሽኙ ስንገላገል የሚቆም ችግር አድርገን እንዳናየው አደራ እላለሁ፡፡ የባሰ ይሆን እንደሆን እንጂ፣ በእርግጥም ደግሞ ተባብሷል፣ ችግሩ ተንሠራፍቶ ያለ፣ በቂ ፍርድ እና ቅጣት ማግኝት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ሳንዘናጋ፤ በአግባቡ ተቀናጅተን በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ለሃገር ጠንቅ ስለሆነ እንደዋንኛ የጋራ ጠላት ልንዋጋው ይገባናል፡፡ የሴት ልጅን መብት ማስከበር የተሳነው ማህበረሰብ የውድቀት እንጂ የስኬት ታሪክ ሊኖረው አይችልምና ሁላችንም እንነሳ፡፡ ደጋግሜ እንዳልኩት ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን፣ የጾታ ጥቃት ተቃውሞ ቀን . . . ወዘተን በዕለታቸው ማክበር እንደተጠበቀ ሆኖ የሴቶችን ጉዳይ በአግባቡ እስካልፈታን ድረስ የ365 ቀናት ተባብረን፣ ተቀናጅተን የምንረባረብበት የቤት ሥራችን ሊሆን ይገባል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.