Fana: At a Speed of Life!

ማይክሮሶፍት በኢንዶኔዥያ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ለመደገፍ ቢሊየን ዶላሮች መመደቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማይክሮሶፍት በኢንዶኔዥያ ከኮምፒዩተር አገልግሎት እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማቶችን ለመደገፍ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ለመመደብ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳቲያ ናዴላ ዕቅዱን ይፋ ያደረጉት ከጥቂት ቀናት በፊት በጃካርታ ባደረጉት ቆይታ በማይክሮሶፍት ግንባታ ዙሪያ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መሆኑ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ አራት ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን÷ የሀገር ውስጥ አጋሮችን ስራ ለማጠናከር በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተዳደር አቅም ለመገንባት እና በዘርፉ በሀገሪቱ ዙሪያ ተበታትነው ባሉ ደሴቶች የተሰማሩ ከ840 ሺህ በላይ ባለሙያዎችን ዕውቀት ለማሻሻል ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው በ29 ዓመታት ውስጥ ለማከናወን ያቀደው የመጀመሪያው ሜጋ ኢንቨስትመንት መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ግንኙነትን ለማሳደግ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ ካሉ ሀገራት ጋርም አስፈላጊ በሆነው ኢኮኖሚ ላይ እምነት እንዳለው ማሳያ ምልክት ነው ብለዋል።

የኢንዶኔዥያ ኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ኤሪ ሴቲያዲ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ በ2045 ወርቃማዋን ኢንዶኒዢያ ለመገንባት ይዘው ለነበረው ፖሊሲ ድጋፍ የሚሆነውን ውሳኔ በደስታ ተቀብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በኢንዶኔዥያ ሰዎች እየሰሩ ያሉበትን መንገድ እና የህዝቡንም ህይወት የሚለውጥ እንደሆነ መናገራቸውን ኤዢያ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የደቡብ ምስራቅ እስያ ቀጣናን ያቀፈ እና ዓመታዊ ገቢን የሚጨምር ከመሆኑም ባሻገር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የስራ እድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.