Fana: At a Speed of Life!

ከሰልን ሲጠቀሙ መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች…

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለይም በበዓል እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ሲኖር ከሰልን በአማራጭ የኃይል ምንጭነት መጠቀም የተለመደ ተግባር ነው፡፡
 
በመሆኑም ከሰልን ሰዎች ለተለያየ አገልግሎት ሲጠቀሙ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
 
ምክንያቱም አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ የከሰሉ ጭስ ሞትን ጨምሮ የዕድሜ ልክ ህመም ለሆኑት የአዕምሮ ጉዳትና የልብ በሽታ ስለሚያጋልጥ ነው ይላሉ፡፡
 
በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም÷ የከሰል ጭስ በዓይን የማይታይና ሽታ አልባ መርዛማ ጋዝ አለው፡፡
 
ይህ ጋዝ የሚፈጠረውም ጋዝ፣ ዘይት፣ ከሰል ወይም እንጨት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው ባለማለቃቸው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
 
የከሰል ጭስ ባለበት አካባቢ አየር ወደ ውስጥ በሚሳብበት ጊዜ÷ በደም ውስጥ በመግባት የቀይ የደም ኅዋስ አካል የሆነውና ኦክስጅን ተሸክሞ ለተያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚያደርሰው ሂሞግሎቢን ጋር በመቀላቀል ጉዳት ያስከትላል፡፡
 
ይህን ተከትሎም ደም ኦክስጅን መሸከሙን ያቆማል፤ በዚህ የተነሳ የኅዋሶቹ አነስተኛ ክፍሎች ይጎዳሉ፤ ብሎም ይሞታሉ፡፡
 
• በከሰል ጭስ (በካርበን ሞኖክሳይድ) የተጠቃ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች
 
የራስ ምታት፣ ራስ ማዞርና መታመም፣ የድካም ስሜትና ግራ መጋባት፣ ሚዛንን ለመጠበቅ መቸገር፣ የዕይታና የትውስታ ማጣት፣ ራስን መሳት፣ በአንድ ነገር ላይ አትኩሮት ማጣት፣ የሆድ ህመም እንዲሁም ለመተንፈስ መቸገር ምልክቶች ሊታዩበት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
• የከሰል ጭስን እንዴት መከላከል ይቻላል?
 
በከሰል ምግብ ማብሰል ሲያስፈልግ በቂ አየር እንዲያገኝ ከተቻለ ከቤት ውጭ ማብሰል፤ ከቤት ውጭ ማብሰል ካልተቻለ ደግሞ ሙሉ በመሉ ከተቀጣጠለና ጭሱ መጥፋቱ ሲረጋገጥ ወደ ቤት ማስገባት ይመከራል፡፡
 
በተጨማሪም የከሰል ምድጃ እየተጠቀሙ በር እና መስኮት አለመዝጋት፣ በከሰል ምግብ አብስለው ሲጨርሱ በውኃ ማጥፋትና በርና መስኮት በመክፈት ቤቱን ማናፈስ እንዲሁም ከሰል ቤት ውስጥ አለማቀጣጠልን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
 
ከዚህ ባለፈም ከሰል ቤት ውስጥ አቀጣጥሎ ማሸለብ ወይም መተኛት አደጋው የከፋ በመሆኑ ከእነዚህ ድርጊቶች ይቆጠቡ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.