Fana: At a Speed of Life!

የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ ነው- በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት÷ተማሪዎችን ወደ ቻይና እና ሩሲያ በመላክ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ማእከል ለመገንባትም ከሩሲያው የኒውክሌር ኩባንያ ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የአዋጭነት ጥናቱ ካለቀ በኋላ የማዕከል ግንባታውን የማከናወን ስራ እንደሚጀመር በመግለጽ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር ሁለት ሳተላይቶችንም ወደ ህዋ እንዳመጠቀች አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ የፈጠራ ሃሳብ ስርዓት ባለው መልኩ ዘላቂነትና ግልጽነት እንዲኖረው ለማስቻል የኢኖቬሽን ስታርታፕ ድጋፍ ማዕከል ማዘጋጀት ትኩረት ተሰጥቶት የተከናወነ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገር ውስጥ በመሆን የውጭ ሀገር ስራዎችን ለመስራት ለተሰማሩ 6 ድርጅቶች ከታክስ ነጻ አገልግሎትና የውጭ ሀገር የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉንም ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

ቴክኖሎጂዎች በአግባቡና በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የጎንዮሽ ጉዳታቸውን ለመቀነስ ሲሰራ እንደነበርም በመግለጽ ለ2 ሺህ 472 የቴክኖሎጂ ቁሶች ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ተቋማቸው የምርምር ስራዎችን እንደሚደግፍ ገልፀው የምርምር ውጤቶችም ችግር የሚፈቱና ማህበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዘርፉ የሚፈልጋቸው አዋጆችና ደንቦች ተቋሙ በሚፈልገው ልክ መጽደቅ አለመቻላቸውና ለቴክኖሎጂ ግዥዎች የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው ደረጃ ማግኘት አለመቻል ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ÷በቀጣይ የምርምር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ የምርምር ውጤት ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት ማለፍ ያለበትን “የሴፍቲ ስታንዳርድ” አሟልቶ ሲያልፍ ለአገልግሎት እንዲውል እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

የሳይበር ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው÷ የዲጂታል ፋይናንስ የክፍያ ስርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

በከተማና በገጠር፣ በወንዶችና በሴቶች እንዲሁም በክልሎችና በከተሞች መካከል በዲጂታል ትስራቴጂው ትግበራ ልዩነቶች እየሰፉ እንዳይሄዱ መስራት እንደሚያስፈልግ እና ይህም ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የዘርፉ አሰራር ጥምረትንና ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው÷ተቋማት እያለሟቸው ያሉ የዲጂታል ሲስተሞችና እየገነቡ ያሏቸው መሰረተ ልማቶች ላይም የክትትልና የድጋፍ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በምክር ቤቱ የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ÷ለፈጠራ ሃሳብ ባለቤት ወጣቶች ድጋፍ በማድረግ በየአካባቢው የሚገኙትን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም እንደሀገር ሃብት መጠቀም እንዲቻል በየክልሎች ማዕከላትን በመክፈት ረገድ ተቋሙ እንዲሰራ ጠቁሟል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.