Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩክሬን ገቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካ ለዩክሬን ያላትን ድጋፍ ለመግለጽ በድንገተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ኪዬቭ ገቡ፡፡

ሌሊቱን ከፖላንድ በባቡር ተጉዘው ኪዬቭ የገቡት ሚኒስትሩ አሜሪካ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ዩክሬናውያን ያላትን ጠንካራ አጋርነት የሚያሳይ ስለመሆኑ ከብሊንከን ጋር የተጓዙ ከፍተኛ ባለስልጣን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ምሥራቅ ካርኪቭ ግዛት አዲስ ዘመቻ የከፈተውን የሩሲያ ጦር ወደ ኋላ ለመመለስ እየተፋለመች ባለችበት ወቅት አሜሪካ ለዩክሬን ያላትን ድጋፍ ለመግለጽ ብሊንከን በድንገተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ኪዬቭ መግባታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

አንቶኒ ብሊንከን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ በዩክሬን ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን÷ የአሜሪካ ኮንግረስ ባለፈው ወር የ61 ቢሊየን ወታደራዊ ማዕቀፍ ድጋፍ ካፀደቀ በኋላ ግን ወደ ኪዬቭ ሲያቀኑ የመጀመሪያቸው መሆኑን ዘገባው አመላክቷል፡፡

በዩክሬን ቆይታቸውም ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪን ጨምሮ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚያገኙና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.