Fana: At a Speed of Life!

የሀብት ምዝበራዎችና ኢ-ሰብዓዊ ጥሰቶች በሚዲያ በመቅረባቸው የተከፉት የተግባሩ ተሳታፊዎች ናቸው- አቶ ንጉሱ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ሲፈጸሙ የነበሩ የሀብት ምዝበራዎች በመገናኛ ብዙሃን በመቅረባቸው የተከፉት የተግባሩ ዋነኛ ተሳታፊዎች መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

አቶ ንጉሱ የሃብት ምዝበራ ተዋንያኖች ብሔርን እንደ ዋነኛ መደበቂያ ምሽግ እየተጠቀሙበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ የተወለደው በዜጎች ላይ ሲፈጸም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሀብት ምዝበራ መባባስን ተከትሎ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ታዲያ የአራተኛ መንግስትነት ሚና ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ይህን ችግር ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ በኢትዮጵያ መጻኢ ታሪክ ውስጥ እንዳይደገም የመስራት ኃላፊነት እንዳለባቸውም አብራርተዋል።

መገናኛ ብዙሃን ይህን ኃላፊነት በሚፈለገው ደረጃ እያከናወኑ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ መገናኛ ብዙሃን የተፈጸመብኝን ግፍ ለህዝብ አላደረሰልኝም በሚል ቅሬታ የሚያሰሙ ሰዎች መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በተቃራኒው የሃገር ሀብት ሲዘርፉና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ቡድኖች ብሔርን እንደ ምሽግ በመጠቀም በመገናኛ ብዙሃን ብሔር ተኮር የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተከፈተ አስመስለው ይናገራሉ ብለዋል።

እነዚህ ቡድኖች ማንኛውንም ብሔርም ሆነ ሃይማኖት እንደማይወክሉ የጠቀሱት ሃላፊው፥ ወክለነዋል የሚሉት ብሔርም ሆነ ሃይማኖት ይህን እውነት እንዳያነሳ የማፈንና የማደናገር ስራ ላይ ተጠምደዋል ነው ያሉት።

መንግስት በህግ ማስከበር ሰበብ የሰብዓዊ ጥሰት እያከናወነ ነው የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርቡበታል በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ፥ የመንግስትን የህግ ማስከበር ጥበብ ጥላሸት ለመቀባት በርካቶች ድራማ እየተወኑ ነው’ ሲሉ ተናግረዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከናወነ የሚለው ድራማ የሚጀምረው በወንጀል ድርጊት ሲሳተፉና ሲመሩ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር ሲውሉ መሆኑንም አውስተዋል።

መንግስት ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በሃይል ሳይሆን በሆደ ሰፊነት በርካታ የህግ ጥሰቶች ላይ ህግን የተከተለ የማስተካከያ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

የለውጡ መምጣት የህዳሴ ግድቡ ላይ ትልቅ ድል እንዲመዘገብ ማድረጉን አስታውሰው፥ ከዚህ አንጻር ግድቡ ተሸጧል የሚሉ የበሬ ወለደ ክሶች መሰረተ ቢስ ናቸው ብለዋል።

የግድቡ ውሃ ሙሊት ሲጀመር በግድቡ ላይ የሚሰነዘሩ አሉባልታዎች እንደሚከስሙ ጠቁመው፥ የህዳሴ ግድብ ዳር እስከሚደርስ ሁሉም ዜጋ በአንድነት እንዲረባረብ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.