Fana: At a Speed of Life!

የዩኒቨርሲቲዎች የፕሮጀክት ወጭዎች ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል -የገንዘብ ሚኒስቴር

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩኒቨርሲቲዎች በጀት በተለይም የፕሮጀክት ወጭዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናሩ በመምጣታቸው ተገቢው ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ አሳሰቡ፡፡

የኮምፕርሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጀት ሰሚ መርሀ-ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት የክላስተር አደረጃጀት 21 የኮምፕርሄንሲቭ፣ ሁለት የሳይንስና ቴክኖሎጅ እንዲሁም ሁለት የልዩ ዩኒቨርሲቲዎች የ2017 በጀት ዕቅድ ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቦ ተገምግሟል፡፡

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማትም የበጀት ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ÷ የዩኒቨርሲቲዎች በጀት በተለይም የፕሮጀክት ወጭዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናሩ በመምጣታቸው ተገቢው ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በአፈጻጸማቸው የተሻሉትን ፕሮጀክቶች ለይቶ ማጠናቀቅ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ኖሯቸው የተቋረጡትን ደግሞ ባሉበት እንዲቆዩ ማድረግ የመጭው ዓመት የበጀት አቅጣጫ መሆኑን መግለፃቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በበጀት ስሚው መርሀ-ግብር የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር በሚመስል መልኩ ከትምህርት ጥራት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ከሌላቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ወጥተው የተመደበላቸውን በጀት በዋናው የመማር ማስተማር ተልዕኳቸው ላይ ሊያውሉት ይገባል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ሃሳባቸውን የሰጡ ሲሆን÷ በሚኒስቴሩ ባለሙያዎች የተሰጣቸውን ዝርዝር አስተያየቶች በማካተት የበጀት ዕቅዳቸውን አስተካክለው በሶስት ቀናት ውስጥ እንዲያቀርቡ ተገልጾላቸዋል፡፡

በተመሳሳይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የ2017 ዓ/ም የበጀት ዕቅድ ቀርቦ ከተገመገመ እና ሰፊ የሃሳብ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ ተቋማቱ በተሠጣቸው ጣሪያ መሰረት፣ የተመደበላቸውን በጀት በቁጠባና ውጤታማነት መርህ፣ ቅድሚያ ለሚሰጡ ጉዳዮች ቅደም ተከተል አስይዘው፣ በሶስት ቀናት ውስጥ ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.