Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ የተወያየባቸው እና ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በ4 የፋይናንስ ድጋፍ እና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘ የ52 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ለስራ ፈጠራ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከጣልያን መንግስት የተገኘ 10 ሚሊዮን ዩሮ፣ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተገኘ 255 ሚሊዮን ዶላር አንዲሁም ለፓወር ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንትና ሞደርናዜሽን ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ማስፈፀሚያ የሚውል 393 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተደረጉ የብድር ናቸው፡፡ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘው ብድር 0.01% ወለድ እና ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጭዎች 0.1% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብበት ሆኖ የ15 ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከጣልያን መንግስት የተገኘው ብድር ከወለድ ነጻ ከመሆኑም በላይ የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለውና በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተገኙት ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች 0.75% የአገልግሎት ክፍያ ብቻ የሚታሰብባቸው፣ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ ሁሉም ብድሮች ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባቀረባቸው 3 ረቂቅ አዋጆች እና 1 ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
የመጀመሪያው የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን መሰረታዊ ከሆኑ መብቶች አንዱ የሆነውን የመዘዋወር ነፃነትን ለማስከበር፣ የኢሜግሬሽን አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያዊንና ለውጭ አገር ዜጎች በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና መስጠት እንዲቻል፣ የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር እና አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የተሟላ የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ሁለተኛው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን በድጋሚ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ስርዓት የሰፈነበት እንዲሆን፣ የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት በሚገባ የሚያስጠብቅ ስልጣንና አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

3. ሶስተኛው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ውጤታማ ማድረግ፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሰረታዊ የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና ለማስከበር ሁሉን አቀፍ የምዝገባ ስርዓት መዘርጋት የሚገባ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረቡት 3 ረቂቅ አዋጆች ላይ በሰፊው ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. አራተኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋት፣ የአገልግሎቶቹን የጥራት ደረጃ ማሻሻል፣ ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ያወጡትን ወጪ መሸፈን የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያያው በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በቀረቡ 2 የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግስታት መካከል ያለውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተፈረመ ስምምነት ነው፡፡ ሌላው ስምምነት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ መንግሥታት መካከል የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቶቹ ቢጸድቁ ኢትዮጵያ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ እና በአገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የሚያጎለብቱ መሆኑን በመገንዘብ፣ የስምምነቶቹ መጽደቅ የአገራችንን ጥቅም የማይጎና የተለየ ግዴታም የማያስከትል መሆኑን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.