Fana: At a Speed of Life!

ሠራዊታችን ያደረጋቸው ስምሪቶች ሕዝቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ አስችሏል ¬- ሌ/ጀኔራል መሀመድ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሠራዊታችን ከአማራ ክልል የጸጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት ያደረጋቸው ስምሪቶች ሕዝቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ አስችሏል ሲሉ የጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ገለጹ።

ኮማንድ ፖስቱ በምስራቅ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ የተልዕኮዎቹን ቁልፍ ተግባር ገምግሞ የፀጥታ ሀይሉና አስተዳደሩ ተቀናጅተው በመስራታቸው የተገኘው ውጤት ክልሉ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማስቻሉን አረጋግጧል።

የተገኘውን ውጤት አስመልክቶ ሌ/ጀኔራል መሀመድ ተሰማ እንዳሉት፤ የተገኘው ውጤት አመርቂ የሆነው የፀጥታ ሀይሉና ሲቪል አስተዳደሩ ተቀናጅተው በመስራታቸው ነው።

ሠራዊታችን ከክልሉ የጸጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት ያደረጋቸው ስምሪቶች ሕዝቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ አስችሏል በማለት ገልጸው፤ የአገልግሎት ተቋማት ስራ መጀመራቸውን፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የማዳበሪያ ስርጭቱ ያለ እንቅፋት መከናወኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ከኮማንድፖስቱ ጋር በመተባበር ለራሱ ሰላም መረጋገጥ መስራቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ጽንፈኛውን ለመደምሰስ በምናደርገው የህግ ማስከበር ግዳጅ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ሰላምን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ተግባር ተኮር ስራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በህዝቡ ውስጥ የተደበቁ የፅንፈኛው ሴሎችን በማውጣት እና እርምጃ በመውሰድ የቀጠናውን ማረጋገጥ የኮማንድ ፖስቱ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን መግለጻቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.