Fana: At a Speed of Life!

የእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና ተደራሽነት ላይ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግበናል ¬- ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና ተደራሽነት ላይ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግበናል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

ፈጠራዎችን መተግበርና ማዝለቅ ለላቀ የእናቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጤና በሚል መሪ ሀሳብ የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸምና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ውይይት በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የጤና ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ የእናቶችንና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን በማከናወን የእናቶች፣ ህጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና ተደራሽነት ላይ አበረታች ውጤቶችን ተመዝግበዋል።

ለዚህም ስኬት የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ በመተግበር ላይ እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህንን ከግብ ለማድረስ ክልሎች፣ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በየዓመቱ የእናቶችና ህጻናትን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል እንዲሁም የጤና አገልግሎቶችን ጥራት ባስጠበቀ መልኩ ለማስቀጠል ከተለያዩ አካላት ጋር እቅዶችን በማውጣትና በማናበብ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በ2030 ዓ.ም ከ100 ሺህ እናቶች መካከል የሚኖረውን የሞት ምጣኔ ወደ 140 ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊው አቶ እንደሻው ሽብሩ በበኩላቸው፤ በክልሉ በዓመት ከ10 ሺህ እናቶች መከካል 870 የሚሆኑት ህይወት የሚያልፍበት ሁኔታ መሻሻሉን ተናግረዋል።

የእናቶችን ጤና ለማስጠበቅ በተደረገ ጥረት ምጣኔውን ከነበረበት 870 ወደ 270 ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የጨቅላ ህጻናት ላይም እንዲሁ በተመሳሳይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ጠቅሰው፤ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በማቱሳላ ማቴዎስ እና መለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.