Fana: At a Speed of Life!

የብራዚልና የደቡብ አፍሪካ መሪዎች በ’ዘለንስኪ የሰላም ጉባዔ’ እንደማይሳተፉ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ባዘጋጁት የሰላም ጉባዔ ላይ እንደማይሳተፉ ተነገረ።

የሰላም ጉባዔው ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችውን ሩሲያን በማግለል የተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።

በፈረንጆቹ ሰኔ 15 እና 16 ቀን 2024 በስዊዘርላንድ የሚካሄደው ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጦርነቱን ለማስቆም ያስችላል በሚል ባቀረቡት የሰላም ፍኖተ ካርታ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚመክር እንደሆነም ተገልጿል።

በጉባዔው የቡድን 7 እና የቡድን 20 ሀገራት፣ ብሪክስና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከ160 በላይ ሀገራት የተጋበዙበት ሲሆን፤ የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነችው ሩሲያ እንድትሳተፍ ግብዣ አልቀረበላትም።

ይህንን ተከትሎም የብሪክስ አባል ሀገሯ ብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ሩሲያን ባገለለው የሰላም ኮንፍረንስ እንደማይሳተፉ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

ሁለቱን ወገኖች ያላሳተፈ የሰላም ጉባዔ ፋይዳ ቢስ ነው ሲሉም መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በጉባዔው እንደማይሳተፉ በቃል አቀባያቸው በኩል ማሳወቃቸውን የአርቲ ዘገባ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.