Fana: At a Speed of Life!

የሴቶች የላይኛው መራቢያ ክፍልን የሚያጠቃ በኢንፌክሽን አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ምንነትና መዘዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የላይኛው የመራቢያ ክፍል ኢንፌክሽን የሚባለው ከማህፀን ጫፍ የውስጠኛው በር በላይ ያሉትን የሴት ልጅ የመራቢያ ክፍሎች የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው፡፡

እነዚህ የሴት ልጅ የመራቢያ ክፍሎችም የማህጸን የውስጠኛው ግድግዳን፣ የማህጸን ቱቦዎችን፣ የሴት የዘር ፍሬ ማምረቻ እጢዎችን እንዲሁም በዙሪያው ያሉ ሌሎች አዋሳኝ የአካል ክፍሎች ናቸው፡፡

የበሽታው ምክንያት ከ85 በመቶ በላይ በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፍ እና በወቅቱ ያልታከመ የአባለዘር በሽታ ነው።

በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከፅንስ መቋረጥ፣ ከወሊድ እና ሌሎች በማህፀን ላይ ከሚሰሩ የህክምና ስራዎች በኋላ ሊከሰት ይችላል።

ይህም የሚሆነው ከላይ በተጠቀሱት የበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች ምክንያት በታችኛው የሴት ልጅ የመራቢያ አካላት ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ባክቴሪያዎች ወደ ላይኛው የሴት ልጅ የመራቢያ አካላት ውስጥ ዘልቀው የመግባት እና የመራባት እድል ሲያገኙ ነው።

በሽታው እንደየባክቴሪያዎቹ ዓይነት እና ባህሪ በፍጥነት ምልክቶችን በማሳየት ቶሎ ሊታወቅ ወይም ምንም ምልክት ሳያሳይ ወይም ቀላል የሚመስሉ ምልክቶችን በማሳየት ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል።

የበሽታው አጋላጭ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?

• ከአንድ በላይ ሰው ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም፣
• የአባላዘር በሽታ ካለበት ሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ፣
• ከ 15-25 አመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ መገኘት፣
• ከዚህ ቀደም በሽታው ከነበረ፣
• ደህንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ … ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ምልክቶቹ

• በታችኛው የሆድ ክፍል የሚሰማ የሆድ ህመም ወይም ቁርጠት፣
• ከማህጸን የሚወጣ ያልተለመደ ወይም ጠረን ያለው ፈሳሽ፣
• ትኩሳት፣
• ማስታወክ፣ ማቅለሽለሽ፣
• የደም መፍሰስ … ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ህመሙ ምልክት ሳያሳይ ለረጅም ጊዜ ከቆየ ወይም በወቅቱ ካልታከመ እስከ መካንነት የሚደርስ ችግር ሊያስከትል ይችላል።

ህክምናው

• ከላይ የተጠቀሱ በበሽታው የመያዝ እድልን የሚጨምሩ ምክንያቶችን ማስወገድ፣
• ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲሰሙ ቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማድረግ፣
• በተጨማሪም በሀኪም የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም በባለሙያ የሚሰጡ ምክሮችን በአግባቡ መተግበር እጅግ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ከአዲስ አበባ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.