Fana: At a Speed of Life!

የደም ግፊትዎን ተለክተዋል?

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ የደም ግፊት መኖር ለአጣዳፊ የልብ ውጋት ወይም በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ስራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል፡፡

ዛሬ የዓለም የደም ግፊት ቀን ሲሆን ቀኑን ስለደም ግፊት ግንዛቤ በመስጠትና ሰዎች የደም ግፊታቸውን በመለካት ያሉበትን የጤና ሁኔታ እንዲያውቁ ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት ለተለያዩ ድንገተኛ ህመሞች የሚያጋልጥ ሲሆን ባስ ካለ ደግሞ የሰውነትን የጤና ስርዓት በማዛባት ለሞት የሚዳርግ የጤና መታወክ ነው፡፡

ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ የሚሆኑት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

• ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ፣ በተለይም ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ፣
• የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ የሆነ፣
• የኩላሊት በሽታ ያለባቸው፣
• የስኳር በሽታ ያለባቸው፣
• የደም ግፊት በሽታ በቤተሰባቸው ታሪክ ያለባቸው፣ ወይም በበሽታው የተጠቃ የቅርብ ዘመድ ካለ፣
• ብዙ ጊዜ የሚጨነቁ፣
• የሰውነት እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ፣
• ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ፣
• የአልኮል መጠጥ የሚያዘወትሩ፣
• ብዙ ጊዜ ጨው የበዛበት ምግብ የሚመገቡ እንዲሁም
• በቂ ፍራፍሬና አትክልት የማይመገቡ ይጠቀሳሉ፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት ሲኖር የህመም ስሜት ወይም ሌሎች ምልክቶች ላይታዩ እንደሚችሉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ የእርስዎም የደም ግፊት መጠን ከፍተኛ ከሆነ እና በጊዜው ህክምና ካላደረጉ ለከፍተኛ የልብ በሽታና በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ስራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድልዎ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገለጻል፡፡

በዚህም የደም ግፊትዎን መጠን ማወቅ ሕይወትዎን ሊያድን ይችላልና የደም ግፊትዎን በየጊዜው እንዲለኩ የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ ይመክራል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.