Fana: At a Speed of Life!

ታዋቂ ግለሰቦች ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታዋቂ ግለሰቦች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የኢጋድ የታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ስብስባ ዛሬ ሲጠናቀቅ ዋና ጸሐፊው÷ የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች በማኅበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

የታዋቂ ግለሰቦቸች ምክር ቤት ኢጋድ በሰላም፣ መረጋጋት፣ ቀጣናዊ ትስስር፣ ሕገ-ወጥ ስደትና የድንበር ጉዳዮች ላይ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን እንዲደግፍ ከአንድ ዓመት በፊት መቋቋሙን አስታውሰው፤ የሚጠበቅበትን ያህል አልሰራም ብለዋል።

ስብሰባው የምክር ቤቱን የመፈጸም አቅም ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከሩን ገልፀው፤ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የምክር ቤቱ ሚናና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የምክር ቤቱ መቋቋም በግጭትና አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት ላስተናገደው ቀጣናው በጎ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ምክር ቤቱ ለሚያደርጋቸው ሁሉን አቀፍ ጥረቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የኢጋድ ታዋቂ ግለሰቦች ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ÷ አፍሪካውያን ለሚገጥሙን ፈተናዎች በራሳችን አቅም መፍትሔ ማበጀት አለብን ሲል ተናግሯል፡፡

ለዚህም ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶቻችንን መጠቀም እንደሚገባና የሀገር ሽማግሌዎችም ከዚህ አኳያ ወሳኙን ሚና እንዲወጡ መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.