Fana: At a Speed of Life!

በአፍጋኒስታን በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የ68 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍጋኒስታን በድጋሚ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የ68 ሰዎች ህይወት ማለፉን የታሊባን ባለስልጣናት አስታወቁ፡፡

በአፍጋኒስታን ከወትሮው የተለየ ከባድ ዝናብ እየጣለ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በዝናቡ ሳቢያ በሰሜናዊ እና ምዕራባዊ አፍጋኒስታን የጎርፍ አደጋ መከሰቱ ተሰምቷል፡፡

በአደጋው በምዕራብ አፍጋኒስታን በሚገኘው የጎሆር ግዛት 50 ሰዎች ሲሞቱ በሰሜናዊ አፍጋኒስታን ደግሞ 18 ሰዎች መሞታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ከሰው ህይወት ማለፍ በተጨማሪ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ በአደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች፣ ከ100 ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳ እና 300 የቤት እንስሳት በጎርፍ መወሰዳቸው ተነግሯል፡፡

አፍጋኒስታንን እየመራ የሚገኘው የታሊባን መንግስት በአደጋው በተጎዱ ሰዎች የተሰማውን ሀዘን ገልጾ፤ የሰብአዊ ድርጅቶች እና አጋር አካላት ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጎርፍ አደጋው በጎሆር ግዛት ብቻ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውን ገልፆ÷ የአለም ምግብ ፕሮግራም የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሰዎችን በአካባቢው ሊያሰማራ መሆኑን ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.