Fana: At a Speed of Life!

“የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ይካሄድ ብሎ መወሰኑ ህገ መንግስቱን የሚጻረር ስለሆነ መንግስት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አክብሮ ያስፈጽማል” – አቶ ንጉሱ ጥላሁን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርጫን የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው በህግመንግስቱ አንቀፅ 102 የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ ስለሆነ ሌላ አካል በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ልግባ ቢል ከስልጣን ገደቡ በላይ የምርጫ ቦርድን ስልጣን መጋፋት እና መዳፈር ስለሚሆን መንግስት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አክብሮ ይፈጽማል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ።
 
መከላከያ ሰራዊቱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ “የሃገርን ሉዓላዊነትና ህገመንግስቱን እንደሚያስከብር ሁሉ ምርጫ ቦርድም የተሰጠውን ህገመንግስታዊ ስልጣን ሁሉም አካል ሊያከብር ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል።
 
ሀላፊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፥ በህገመንግስቱ መሰረት ምርጫን የማስፈጸም ስልጣን ለአስፈጻሚው ስላልተሰጠ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ነገር ሊያደርግ የሚችለውና ህገመንግስታዊ ስልጣን ያለው ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው፡፡
 
“አስፈፃሚ አካሉ በምርጫ ቦርድ ስራ እና ውሳኔ ጣልቃ በመግባት ቢፈትፍት ያለ ሀላፊነቱ መንቀሳቀስ ስለሆነ መንግስት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ያከብራል፣ ይፈፅማል” ነው ያሉት አቶ ንጉሡ፡፡
 
በኢትዮጵያ ታሪክ ምርጫ ቦርድ የተሻለ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋምና ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መጎልበት በር እንዲከፍት ሆኖ ተደራጅቷል ያለት አቶ ንጉሡ፥ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ልግባ ቢል ከስልጣን ገደቡ በላይ የምርጫ ቦርድን ስልጣን መጋፋት እና መዳፈር ይሆናል ሲሉ ነው ያብራሩት።
 
እንደ አቶ ንጉሡ ገለጻ፥ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ትኩረቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል የህዝብን ደህንነት መጠበቅ፣ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚገጥመን የማደነቃቀፍ ፈተና በማለፍ ውሃ መሙላት መጀመር እና ለጥቅም ማብቃት እንዲሁም ወረርሽኙ ሊያደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሊቀንሱ የሚችሉ ስልቶችን ነድፎ መረባረብ ነው፡፡
 
የምርጫው ጉዳይ ገለልተኛው እና በህገመንግስቱ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ስራ ይሆናል ያሉት አቶ ንጉሡ፥ ምርጫ ቦርድ ደግሞ በህገ መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሚያደርገውን ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ አስታውቃዋል።
 
ይህም ልክ መከላከያ ሰራዊቱ ገለልተኛ ሆኖ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ህገመንግስቱን እንደሚያስከብር ሁሉ ምርጫ ቦርድም በህገመንግስቱ የተሰጠውን ስልጣንና ሃላፊነት ያስከብራል ማለት እንደሆነ አብራርተዋል።
 
የትግራይ ክልል ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት የክልሉን ምክር ቤት ምርጫ በዘንድሮው አመት እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.