Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ለደብረ ብርሃን ደነባ – ለሚ መገንጠያ እና ጅሁር – ደነባ የአስፓልት መንገድ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ደነባ – ለሚ መገንጠያ እና ጅሁር – ደነባ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

አጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ 108 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ለግንባታው የሚወጣው 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው ተብሏል።

የመንገዱ ትከሻን ሳይጨምር የጎን ስፋት 7 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባ ሲሆን የስትራክቸር፣ የአነስተኛ ማፋሰሻ ቱቦ እና ድልድዮች ስራዎችን እንደሚያካትት ተጠቁሟል።

ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የመንገድ ግንባታውን በአስፓልት ደረጃ ለመገንባት የተረከበ ሲሆን ግንባታው በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ቀነ ገደብ ተቀምጦለታል።

በጠጠር ደረጃ ብዙ አመታትን የቆየውና ለትራንስፖርት አመቺ ያልነበረው መንገዱ ወደ አስፓልት ደረጃ እንዲያድግ ለዓመታት ጥያቄ ሲነሳበት የቆየ ነው።

የመንገዱ መገንባት በአካባቢው ይስተዋል የነበረውን የትራንስፖርት መጉላላት ችግር በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል።

መንገዱ በባሶና ወራና፣ እንሳሮ፣ አብቹና ኘአ፣ ሲያ ደብርና ዋዩ እንዲሁም ሞረትና ጅሩ የሚገኙ ከ500 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።

በፕሮግራሙ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል፣ የክልልና የዞን የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በደብረብርሃንና አካባቢው የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ከፍተኛ አመራሮቹ ጉብኝታቸውን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በሚያስተምረው ሃይሌ ሚናስ አዳሪ ትምህርት ቤት እና የደብረ ብርሃን ተርሸሪ ሆስፒታል፣ የአንኮበር መንገድን ጨምሮ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ነው የጎበኙት።

በሰላም አሰፋ

ተጨማሪ መረጃ ከኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.