Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ እና ኢራቅ በወታደራዊ ጉዳዮች በጋራ መስራት በሚችሉበት አግባብ ዙሪያ ምክክር አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ኢራቅ በወታደራዊ ጉዳዮች በጋራ መስራት በሚችሉበት አግባብ ዙሪያ ምክክር አደረጉ።

የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የአሜሪካ ወታደሮች ወደፊት በኢራቅ በሚኖራቸው ቆይታና በሚሰፍሩበት ሁኔታ እንዲሁም በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት በሚችሉበት አግባብ ላይ መወያየት የሚያስችል ምክክር አድርገዋል።

ምክክሩ በዋናነት ከፈረንጆቹ 2014 በኋላ በኢራቅ የሰፈሩ የአሜሪካ ወታደሮችን እጣ ፈንታ፣ ፀጥታና ደህንነት፣ ፀረ ሽብርተኝነት፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ሃገራቱ በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።

በዚህም አሜሪካ ከወታደራዊ ድጋፉ ጎን ለጎን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና ዓለም አቀፍ ድጋፎችን ለማስገኘት የኢኮኖሚ አማካሪዎችን መድባለች።

በምክክሩ ላይ ዋሽንግተን በኢራቅ የሚገኙ ወታደሮቿን ቁጥር መቀነሷን እንደምትቀጥል ማረጋገጫ መስጠቷ ተገልጿል።

ከምክክሩ በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫም አሜሪካ በኢራቅ ተጨማሪ ወታደራዊ ጣቢያ የመገንባትም ሆነ የወታደሮቿን ቁጥር የመጨመር ፍላጎት እንደሌላት አስታውቀዋል።

አሜሪካ በኢራቅ ያላትን ተፅዕኖ እቀንሳለሁ ብትልም አሁን ላይ በኢራቅ ካለው የሰርጎ ገቦች ጥቃትና የደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ፥ ወታደራዊ ስልጠናን ጨምሮ በደህንነት እና ፀረ ሽብር ዘመቻዎች አሁንም ድጋፍ ታደርጋለች።

የኢራቅ ፓርላማ ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ የሃገሪቱ መንግስት በሃገሪቱ የውጭ ሃገር ጦር ጣልቃ ገብነት እንዲያስቆም የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ይሁን እንጅ የኩርድ ህግ አውጪዎች እና የተወሰኑ የሱኒ ሙስሊም የፓርላማ አባላት ውሳኔውን ተቃውመው መውጣታቸውም የሚታወስ ነው።

የባግዳድና ዋሽንግተን ግንኙነት አሜሪካ በኢራቅ አውሮፕላን ማረፊያ የኢራኑን ብሄራዊ አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ ቃስም ሶሌይማኒን በድሮን ጥቃት ከገደለች ወዲህ ውጥረት ነግሶበት ቆይቷል።

ትናንት የተደረገው ምክክርም የረገበውን ግንኙነት ማደስ የሚያስችል ሰፊ ውይይት ማድረግ የሚያስችልን መንገድ መክፈትን ያለመ ነው።

ባግዳድ ከአሸባሪው አይ ኤስ ጋር በምታደርገው ጦርነት ለኢራቅ ጦር ድጋፍ ለመስጠት በሚል በኢራቅ ከ5 ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደሮች መስፈራቸው ይታወቃል።

ምንጭ፦ ሺንዋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.