Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ሳዑዲን ወታደራዊ ትብብር ለማሳደግ ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ ዓረቢያን ወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ ውይይት በሳዑዲ ዓረቢያ ተካሂዷል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የተመራ ከፍተኛ የወታደራዊ ልዑክ በሳዑዲ ዓረቢያ የጦር ኃይሎች መረጃ ኤጄንሲ ዋና ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ሁሳም ቢን አብደላ አል ዳመሪ በተደራገለት ግብዣ መሰረት የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡

ከጉብኝቱ ጎን ለጎን በተደረገ ውይይት÷ የሀገራቱ መከላከያ ኃይሎች በወታደራዊ መረጃ ልውውጥ፣ በአቅም ግንባታ፣ በቴክኒክ ትብብርና ድጋፍ ዙሪያ በጋራ የሚሠሩባቸው መስኮች ተለይዋል፡፡

እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መምከራቸውን በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጋራ የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተም ተወያይተዋል።

በተቋማቱ መካከል የሚደረገው ትብብርና መደጋገፍ በሀገራቱ መካከል ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረውን ታሪካዊ ትስስርና ወዳጅነትን መነሻ ያደረገ መሆኑንም ጄኔራል መኮንኖቹ ገልፀዋል።

ጄኔራል ጌታቸው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ከሮያል ሳዑዲ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፋይደይ ቢን ሐሚድ አል-ሮዋይሊ ጋርም ተወያይተዋል።

በቀሪ ቀናትም የተመረጡ የሀገሪቱ ወታደራዊ ተቋማትን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.