Fana: At a Speed of Life!

ለሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደርና ፏፏቴ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ላገኘው ሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ፏፏቴ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ የሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደርን፣ በሁለት ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውን የሌጲስ ፏፏቴ፣ በመንደሯ ውስጥ የሚገኘውን የዕደ-ጥበብ ማምረቻና መሸጫ ቦታ እንዲሁም የላንጋኖ ሐይቅን ጎብኝቷል።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ይህ ውብ ተፈጥሮ የዓለም ሐብት በመሆኑ መንግሥት ትኩረት እንደሚሰጠው ያመላከተው ቋሚ ኮሚቴው÷ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ የተነሱትን መንገድን ጨምሮ የመሰረተ-ልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ላሉ የመንግሥት አካላት እንደሚያቀርብ መገለጹን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ከነጌሌ አርሲ ከተማ በስተምሥራቅ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር በዓለም ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

በአስደናቂ ዕይታዎች፣ ፏፏቴ፣ አዕዋፋት እና የዱር እንስሳት በውስጡ የያዘው የሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር ከቀርከሃ በሚሠሩ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች በስፋት ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዓለም ድንቅ መንደርነት የጮቄ ተራራ እና የወንጪ የኢኮ ቱሪዝም መንደርን ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.