Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በጎንደር ከተማ ሲያካሂድ የነበረውን የተባባሪ አካላት ስልጠና አጠናቀቀ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል በጎንደር ክላስተር በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቋል፡፡

ኮሚሽኑ ከግንቦት 7 ቀን እስከ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጠው ስልጠና በጎንደር ክላስተር ስር ከሚገኙ 75 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ500 በላይ ተባባሪ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም÷ ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት አዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በ10 ክልሎች ተሳታፊዎችን ለይቷል፤ ሌሎች በርካታ ውጤታማ ተግባራትንም አከናውኗል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያከናወናቸውን ተግባራት በአማራና በትግራይ ክልሎች ሳያከናውን መቆየቱን ጠቅሰው፤ ለዚህም ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ጦርነትና በመሣሪያ የታገዙ ግጭቶች መሆናቸው አስረድተዋል፡፡

በምክክር ሂደቱ በየደረጃው ተሳታፊ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ የመለየቱ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በስልጠናው የምትሳተፉ ተባባሪ አካላት ሃላፊነት አለባችሁ ሲሉ ማስገንዘባቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሀገራዊ ምክክርን ምንነትና አስፈላጊነት፣ የኮሚሽኑ የእስካሁን የስራ እንቅስቃሴና የወደፊት ትኩረቶች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች አመራረጥ እና የባለድርሻ አካላት ሚና የሚሉት ጉዳዮች በስልጠናው ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.