Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባን የቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ተሞክሮ ወስደን መሥራት ይገባል – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባን የቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ተሞክሮ በመውሰድ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መስራት አስፈላጊ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

አቶ እንዳሻው ጣሰው በክልሉ በቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ማስጀመሪያ ላይ ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ከፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም በሕጻናት ሁለንተናዊ እድገት፣ ጤና እና ትምህርት ላይ የላቀ ሚና እንዳለው አቶ እንዳሻው ጠቁመዋል።

ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠው÷ የአዲስ አበባን የቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ተሞክሮ በመውሰድ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በቀዳማይ የልጅነት ልማት ፕሮግራም ላይ በማተኮር መስራት የሀገራችንን የትውልድ እጣ ፈንታ ለመወሰን ያስችላል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በውይይቱ በቀዳማይ የልጅነት ፕሮግራም አተገባበር ላይ ያተኮረ የመወያያ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን÷ ለሕጻናት ምቹ የመማሪያ እና የማቆያ ማዕከላት በማዘጋጀት የወደፊት እድገታቸውን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.