Fana: At a Speed of Life!

አቶ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል፡፡

የክስ መቃወሚያቸውንና የዐቃቤ ህግ አስተያየትን መርምሮ ውድቅ ያደረገው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

ችሎቱ ዛሬ በዋለው ቀጠሮ አቶ ታዬ ያቀረቡት ‘‘ክሱ ይሻሻልልኝ’’ ጥያቄን የያዘውን የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ መርምሮ ክሱን ለማሻሻል የሚያስችል የህግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ከዚህም በኋላ አቶ ታዬ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት ከጠበቆቻቸው ጋር ተማክረው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በዚህም “የጻፍኩት ጽሁፍ ፕሮፖጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም” በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ታዬ ዐቃቤ ህግ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ብቻ ብሎ በክሱ መጥቀሱን ገልጸው፥ የኦሮሚያ ምክር ቤት አባልና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነኝ በማለት ‘‘ይህም ተካቶ ይስተካከልልኝ’’ በማለት አመልክተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ አቶ ታዬ ክደው የተከራከሩ መሆኑን ተከትሎ ማስረጃዎችና ምስክሮች እንዲሰሙለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ታዬ እጃቸው ላይ አለብኝ ባሉት አለርጂክ ምክንያትም “እጄ ላይ ካቴና እንዳይደረግ ይታዘዝልኝ” በማለት አመልክተዋል።

በተጨማሪም አቶ ታዬ ተይዞብኛል ያሉት ረቂቅ መጽሀፍ፣ ሁለት ሞባይሎች እና አንድ ታብሌት እንዲመለስላቸው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም በአቤቱታቸው ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሽ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን ማለትም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስትና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኖችና የፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ ፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በስማቸው በከፈቱት ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሲያስተላልፉ ነበር የሚል ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽ ከሁለት የክላሽ ካዝና ከ60 የክላሽ ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.