Fana: At a Speed of Life!

መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር የሚደረግባቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለመወሰን እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይነት ምክክር የሚደረግባቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለመወሰን የምክክር መድረክ እያካሄዱ ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አደም ፋራህ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር አጀንዳዎችን ለመለየትና የምክክር ሂደቱን ለመወሰን እየተወያዩ ነው።

አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ ውይይቱ በመንግሥትና በፓርቲዎች መካከል የትብብር ባህልን ለማጠናከርና ጤናማ የፖለቲካ ፉክክርን ለመትከል የሚያስችል ነው።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲደግፉ ምቹ ምኅዳር እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ሀገራዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ የስትራቴጂ ጉዳዮችን መለየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር  ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች ለመለየት ዛሬ የመጀመሪያው ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመድረኩ ዓላማ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር፣ ከተቋማትና ከክልሎች ጋር በሚደረጉ ውይይቶች የሚቀርቡ አጀንዳዎችን መለየትና ምክክር የሚደረግባቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለመወሰን መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.