Fana: At a Speed of Life!

ተቋሙ ከይዞታ ማረጋገጫ፣ ከመሰረተ-ልማት ስርቆትና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከይዞታ ማረጋገጫ፣ ከመሰረተ-ልማት ስርቆትና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮችን እንዲፈታለት ሸገር ከተማ አሥተዳደርን ጠየቀ፡፡

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) ከከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም “በከተማ አሥተዳደሩ ክልል የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ይዞታዎች ከፍተኛ የመሬት ግብር ክፍያ ቀርቦባቸዋል፤ አንዳንዶቹም ግብር ከተከፈለባቸው በኋላ ድጋሚ ግብር ተጠይቆባቸዋል” ሲሉ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች አንስተዋል፡፡

ለግሪዱ ስጋት የሚሆኑና ለተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ ምክንያት የሆኑ ስርቆቶች እየተፈፀሙ መሆኑንም ገልጸው÷ ከተማ አሥተዳደሩ የተሰረቁ የኃይል ተሸካሚ ብረቶችን በመቆጣጠር በዘራፊዎች ላይም ተመጣጣኝ ርምጃ በመውሰድ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

ለዓመታት ያልተጠናቀቁ የይዞታ ማረጋገጫ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙም ተቋሙ አስተዳደሩን ጠይቋል፡፡

ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ አስተዳደሩ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ከያዘው ዕሴት ጋር የሚጋጩ ጉዳዮችን በመለየት እንዲስተካከሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ጉዳይ በተለየ ሁኔታ እንደሚመለከቱ ገልጸው÷ የተጠቀሱትን ችግሮች በፍጥነት ለመፍታት ኮሚቴ እንደሚቋቋም መናገራቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡

ከስርቆት ጋር የተነሱትን ጉዳዮችንም ወደ ወረዳዎች በመውረድ እና ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙት አዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች መሆናቸውን ገልጸው መሰረተ-ልማቱን በትኩረት መጠበቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኃላፊዎቹ የተጀመረው ግንኙነት በፍጥነት ወደ መሬት እንዲወርድ የጋራ ኮሚቴዎች እንዲዋቀሩና አሰራሩን ሕጋዊ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.