Fana: At a Speed of Life!

ጓደኛቸውን በመግደል የሚያሽከረክረውን መኪና ወስደው ተሰውረዋል የተባሉ ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጓደኛቸውን በመግደል ሲያሽከረክረው የነበረውን መኪና ወስደው ተሰውረዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በ24 ሰዓታት ውስጥ ተይዘዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሰሜን ማዘጋጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ ገ/ሚካኤል ሰይፉ የተባለው ሟች የወንጀል ፈፃሚዎቹ የቅርብ ጓደኛ በመሆኑ በየዕለቱ እየተገናኙ አብረው የሚውሉ፣ የሚዝናኑ እና በእጅጉ የጠነከረ ጓደኝነት ያላቸው የሱሉልታ ከተማ ነዋሪዎች እንደሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።

በዕለቱ ሟች በወንጀሉ ከተጠረጠሩት ከሁለቱ ጓደኞቹ ጋር አብሮ ሲዝናና እንዳመሸም ነው የተነገረው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ቴዎድሮስ ታከለ እና ሲሳይ ጥላሁን ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ የጓደኛቸውን አንገት በማነቅ ህይወቱ እንዲያልፍ ካደረጉ በኋላ አስክሬኑን መንገድ ላይ በመጣል ሞባይል ስልኩንና መታወቂያውን ጨምሮ በወቅቱ ሲያሽከረክረው የነበረውን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 4-15624 ኢት መኪና ወስደው ተሰውረዋል ተብሏል፡፡

ፖሊስ የወንጀሉ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ ባደረገው ያልተቋረጠ ክትትል ወንጀሉን በመፈጸም የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ለይቶ በማወቅ በ24 ሰዓታት ውስጥ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተሰምቷል፡፡

አንደኛው ተጠርጣሪ ከአየር ጤና አካባቢ የተያዘ ሲሆን፥ ሁለተኛው ተጠርጣሪ ደግሞ ሱሉልታ ከተማ ውስጥ መገኘቱም ነው የተነገረው፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ስራ የሰረቁትን ተሽከርካሪ በሸገር ከተማ ወለቴ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ በመውሰድ እንዲሸጥላቸው ለአንድ ግለሰብ እንደሰጡት በማረጋገጥ መኪናው ከቆመበት በምሪት እንዲመለስ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ተሽከርካሪውን ለመሸጥ ተስማምቶ ከተጠርጣሪዎቹ የተቀበለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የክትትል እና የምርመራ ስራው የቀጠለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.