Fana: At a Speed of Life!

የትጥቅ ግጭቶችን ማስወገድ ንፁኃንን ለመጠበቅ የተሻለ መፍትሄ መሆኑን ቻይና አስገነዘበች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትጥቅ ግጭቶችን ማስወገድ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ የተሻለው መፍትሄ ነው ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የቻይና ቋሚ መልዕክተኛ ፉ ኮንግ ተናገሩ።

የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ የዜጎችን ጥበቃ በተመለከተ የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ የቻይና ቋሚ መልዕክተኛ ፉ ኮንግ፤ በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ ህይወትን ማዳን ጥሩ ግብ ቢሆንም ግጭቶች ካልቆሙ የዜጎች ህይወት የማያቋርጥ ስጋት ውስጥ እንደሚወድቅ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ተቀዳሚ ኃላፊነትም የዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ መሆኑን መዘንጋት እንደሌለበት ጠቁመዋል።

በጋዛ ለወራት የዘለቀው ጦርነት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የንፁኃን ጉዳት እና ሰብዓዊ እልቂት ማስከተሉንም አንስተዋል፡፡

እኛ እየተነጋገርን ባለንበት በዚህ ሰዓት በራፋህ ለመጠለል የተሰባሰቡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች በሞት አፋፍ ላይ ናቸው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በጋዛ አፋጣኝ እና ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት በአስቸኳይ ማመቻቸት እንዳለበት ገልጸው፤ ንፁኃንና የንፁኃን መሰረተ ልማቶች የወታደራዊ ዘመቻ ዒላማ መሆን የለባቸውም ሲሉ አስገንዝበዋል።

ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህግ ሊከበር የሚገባው የመጨረሻ መስመር ነው ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡

እንደ ምግብና መድሃኒት ያሉ መሰረታዊ ሸቀጦች እንደ ጦር መሳሪያ ሊያገለግሉ አይገባም፤ ሰብዓዊ ድጋፍም ፖለቲካዊ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ንግድ የሚተዳደርበት ሥርዓት እንዲጠናከርም ቻይና ጥሪ ማቅረቧን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

እያደገ የመጣው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መሳሪያ ጦርነት ላይ የመዋል ስጋትም ይበልጥ ሊጤን እንደሚገባው በመግለጽ ፉ ኮንግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.