Fana: At a Speed of Life!

ያልተቆራረጠ የካንሰር የመድሃኒት አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያልተቆራረጠ የካንሰር የመድሃኒት አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የካንሰር መድሃኒቶችን አቅርቦት ለማሻሻል ያለመ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሄዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ድጉማ በዚህ ወቅት እንደገለፁት÷ እንደ ካንሰር እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡

ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግና የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባትን ተደራሽ ማድረግ በሽታውን ለመከላከል ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛዋ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው÷ በካንሰር ዙሪያ ከ6 ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ጋር በተደረገ ስምምነት የጨረር ህክምና የማስፋፋት ስራ መሰራቱንና ግንባታና ማሽን ተከላው ተጠናቆ በከፊል ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የማህፀን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ መከላከያ ክትባት፣ ምርመራና ህክምና በ1 ሺህ 400 የመንግስት ጤና ተቋማት እየተሰጠ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት በየዓመቱ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የመድሃኒት ወጪን ለመደጎም ከፍተኛ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ያልተቆራረጠ የመድሃኒት አቅርቦት እንዲኖር ከመስራት ጎን ለጎን የባለድርሻ አካላት ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ÷ ያልተቆራረጠ የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳካት የካንሰር መድሃኒቶች አቅራቢ ድርጅቶች ፍላጎት ዝቅተኛነትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት አግልገሎቱ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ ጠቅሰው÷ ተቋማት ለሚገዙት መድሃኒት ሃላፊነት የሚወስዱበት አሰራርና ጤና ተቋማት ያላቸውን ግብዓት ለመጋራት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.