Fana: At a Speed of Life!

የብድር ጫናን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ግሽበትን ለማውረድ፣ የብድር ጫናን ለመቀነስና የውጭ ኃብት ግኝትን ለማሳደግ የሚበረታቱ ተግባራት መከናወናቸውን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የገንዘብ ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ÷ ለማዳበሪያ ግዥ የተላለፈ ድጎማ፣ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ከቀረጥና ታክስ ነፃ መደረጋቸው ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዋጋ ግሽበት እንዳይባባስ ከቦንድ እና ከመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ 88 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር 57 ቢሊየን ብር ተወስዶ ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ ውሏል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ በንብረት ታክስ፣ በተጨማሪ እሴት ታክስና ሌሎችም ላይ እየተደረጉ ያሉ የታክስ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን አብራርተዋል።

ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ብድር 65 ቢሊየን ብር ክፍያ መፈጸሙንም ጠቅሰው፤ የወጪ በጀት አፈጻጸምን በተመለከተ በዘጠኝ ወራት ለፌደራል መሥሪያ ቤቶች 425 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለመክፈል ታቅዶ 309 ቢሊየን ብር መከፈሉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ ለዘጠኝ ወራት የታቀደ ክፍያ 157 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሲሆን፤ 163 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ተፈጽሟል ብለዋል።

የሚኒስትሩን ሪፖርት ያደመጠው ቋሚ ኮሚቴው በተለይም የዋጋ ግሽበት፣ በፊስካል ፖሊሲ፣ በወጪ በጀት፣ በማዕቀፍ ግዥ፣ በኦዲት ግኝትና ሌሎችም ዙሪያ ጥያቄና አስተያየት ሰጥቷል።

የተቋሙ ኃላፊዎች በምላሽና ማብራሪያቸው በተለይም በኦዲት ግኝት ላይ ማስተካከያ የማያደርጉ ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ተጠያቂ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ÷ በአቅም ግንባታ፣ ፊስካል ፖሊሲን በማመንጨትና የኢኮኖሚ ማነቆዎችን እየፈቱ በመሄድ ረገድ ጥሩ ውጤቶች መታየታቸውን ገልፀዋል።

የዋጋ ግሽበትን ለማውረድ እየተደረገ ያለው ጥረት፣ የብድር ጫናን ለመቀነስና የውጭ ኃብት ግኝትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።

በምጣኔ ኃብት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስና እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ እየተወሰዱ ያሉ የፊስካልና የሞኒተሪንግ እርምጃዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

በዚህም በማዳበሪያ ድጎማ፣ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተነሳው የቀረጥና ታክስ፣ የበጀት ጉድለትን ለመሸፈን የተወሰዱ እርምጃዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የዕዳ ጫናን በመቀነስ፣ የውጭ ብድርን እየከፈሉ በመሄድና የክፍያ ጊዜዎች እንዲራዘሙ በመነጋገር የሚደረጉ ጥረቶችንም አድንቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.