Fana: At a Speed of Life!

በፓሪስ ኦሊምፒክ  ዳያስፖራዎች በውድድሩ ቦታ ተገኝተው አትሌቶችን እንዲያበረታቱ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓሪስ ኦሊምፒክ ከ200 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በውድድር ስፍራ ተገኝተው አትሌቶችን እንዲያበረታቱ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል ጠንካራ ስራ እየተሰራ እንደሆነ የፓሪስ ኦሎምፒክ የብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴ አስታውቋል።

ኮሚቴው በተሰጠ መግለጫ፤ ኢትዮጵያን የሚመጥን ውጤት ለማስመዝገብ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጿል።

የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፤ በውድድሩ ከ200 ሺህ በላይ ዳያስፖራዎች በስፍራው ተገኝተው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን እንዲያበረታቱ ለማድረግ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፤ ዕጩ አትሌቶች ከሚያዚያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሆቴል ገብተው ልምምዳቸውን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጻለች።

የ10 ሺህ ሜትር ወንድና ሴት፣ የ1 ሺህ 500 ሜትር እና የ800 ሜትር ወንድ አትሌቶች በስፔን ማላጋ በሚካሄደው የኦሎምፒክ መግቢያ ሰዓት ላይ እንደሚለዩ ጠቁማለች።

በተጨማሪ የማራቶን ቡድኑ የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች ከነተጠባባቂ ተለይተው ልምምድ መጀመራቸውን አንስታለች።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ የስራ አመራሮች እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ ለፓሪሱ ኦሎምፒክ  ስኬት ጠንክረው እየሰሩ መሆኑንም አመልክታለች።

በወርቅነህ ጋሻሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.