Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃ የሚያራግቡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል የሰላም ሁኔታ እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አመራሮች እና በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ተገቢ ያልሆኑ መረጃዎችን የሚያራግቡ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የክልሉ መንግሥት አሳሰበ፡፡

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አባላት የሕዝብ ውክልና ሥራ ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩም የክልሉ ምክር ቤት አባላት እስከታች በመውረድ ችግሮችን በመለየት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር መወያየታቸውንና የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

አባላቱ ባቀረቡት ሪፖርትም በአብዛኛው አካባቢ የፀጥታ ችግር መኖሩን ተከትሎ በርካታ ትምህርት ቤቶች አለመከፈታቸው እና በተመሳሳይ በጤናው ዘርፍም ችግሮች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በመሰረተ-ልማት፣ በመልካም አሥተዳደር፣ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በንግዱ ዘርፍ ያሉ ችግሮች ተቀርፈው ሕብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚነቱ መረጋገጥ መቻል እንዳለበት ተጠቁሟል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ባንቻየሁ ድንገታ÷ ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በቁርጠኝነት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

ከቀረቡት ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ተለይተው ወደ መፍትሔ መገባት እንዳለበት መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ በክልሉ የፀጥታ ችግር ሥራዎችን ለመሥራት እንቅፋት መሆኑን የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ÷ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ሰላም ሁኔታ እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አመራሮች መኖራቸውን ጠቁመው÷ በፌስቡክ፣ ዩቲዩብ እና በቲክቶክ አላስፈላጊ ወሬዎችን የሚያናፍሱ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.