Fana: At a Speed of Life!

አሽከርካሪዎችና ረዳቶችን እያስፈራሩ መኪኖችን ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሽከርካሪዎችና ረዳቶችን በጦር መሳሪያ እያስፈራሩና ጫካ ውስጥ በገመድ እያሰሩ መኪኖችን ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች እስከ 19 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

ለውንብድና ተግባር በቡድን በመደራጀት የሁለት አይሱዙና የአንድ ሲኖ ትራክ ተሽከርካሪዎች ሹፌርና ረዳትን በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ጫካ ውስጥ እግርና እጃቸውን በማሰር ተሽከርካሪዎች በመዝረፍ ተግባር የተሰማሩ አራት ግለሰቦች ናቸው በእስራት እንዲቀጡ የተወሰነው።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት 1ኛ ተገኑ አስታጥቄ፣ 2ኛ ምትኩ ሹሪ፣ 3ኛ አደፍርስ ጣሰው 4ኛ አበበ ደርሴ በተባሉ ተከሳሾች ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችንና የግራ ቀኝ ክርክሮችን መርምሮ በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔ የሰጠው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የምስራቅ ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ 671 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህም አንደኛው ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾቹ ከሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ለውንብድና የወንጀል ተግባር በቡድን በመደራጀት፣ የጦር መሳሪያ በመያዝ በየካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ በኤጀርሳ ቀበሌ ለስራ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲኖትራክ ተሽከርካሪን በማስቆም ሹፌሩና ረዳቱን በጦር መሳሪያ አስፈራርተው ወደ ጫካ በመውሰድ እግርና እጃቸውን በገመድ አስረው በማስቀመጥ ተሽከርካሪውን ዘርፈው ተሰውረዋል።

በሁለተኛ ክስ በየካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በተመሳሳይ ምሽት ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ ቢዮ ቀበሌ የጭነት አይሱዙ የተሽከርካሪ ሹፌርና ረዳትን በግድ እጅና እግራቸውን አስረው ጫካ ውስጥ ጥለዋቸው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ መሆኑ ተጠቅሷል።

በሶስተኛ ክስ ደግሞ በመጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ሌሊት ላይ ከምንጃር አዳማ ማሾ እህል ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ ተሽከርካሪን በማስቆም ሹፌርና ረዳቱን እጅና እግራቸውን በገመድ አስረው ጫካ ውስጥ በማስቀመጥ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ተሽከርካሪውን ከነጭነቱ ዘርፈው ተሽከርካሪውን ደንቢዶሎ ወስደው በደበቁበት በፀጥታ አካላት ክትትል ተሽከርካሪውና ሁሉም ተከሳሾችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው በክሱ ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር እንዲደርሳቸው እና ክሱ በንባብ እንዲሰማ ከተደረገ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው ክደው ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም ማስረጃዎችን መርምሮ የወንጀል ድርጊቱ መፈጸሙን በማረጋገጥ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መንገድ ማስተባበል አለመቻላቸው በችሎቱ ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየትና የተከሳሾቹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።

በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽን በ19 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽን በ16 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት፣ 3ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 4ኛ ተከሳሽን በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.