Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ቀጣዩን የ “አይ ዲ 4 አፍሪካ” ጉባዔን እንድታስተናግድ ተመረጠች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ2025 የሚካሄደውን የ “አይ ዲ 4 አፍሪካ” ጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ሀገር ሆና ተመረጠች፡፡

የ “አይ ዲ 4 አፍሪካ” ሊቀ መንበር ጆሴፍ ጄ ሃቲክ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ-ኬፕታወን እየተካሄደ በሚገኘው የድርጅቱ የ2024 ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ የቀጣዩን ዓመት ጉባዔ እንድታስተናገድ መመረጧን አብስረዋል፡፡

በጉባዔው የተገኙት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ቀጣዩን ጉባዔ እንድታስተናግድ በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማስተናገድ በሙሉ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መቀበሏንም አረጋግጠዋል፡፡

የሀገራችን መመረጥ የዲጅታል መታወቂያ ዘርፍን ጨምሮ ሁለንተናዊ ልማትን ለማሳለጥና ለማሳካት መሰረት የሆነውን የዲጅታላይዜሽን መሰረተልማት ዝርጋታና ትግበራ በቁርጠኝነት እያደረገች ላለው ጥረትና እየተመዘገ ላለው ስኬት እውቅና የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ በዘርፉ የሀገራችንን በስኬት የታጀበ እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ በማስገባትና በመንግስታችን ላይ እምነት በማሳደር የአስተናጋጅነት ዕድሉን ስለሰጠን ለሕዝባችን ከፍተኛ ኩራትና ደስታ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የድርጅቱን አመራሮች አመሥግነው፤ ለጉባዔው ስኬት መንግስት በበቂ ዝግጅት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣዩ ጉባዔ ላይም ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት መናገሻቸው ወደ ሆነችው አዲስ አበባ በመምጣት እንደሁል ጊዜው ሁሉ ስኬታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግብዣ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማስተናገድ መመረጧን ተከትሎም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርያስላለሴ የተመራው ልዑክ አባላት በኬፕታወኑ ጉባዔ ላይ በጋራ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

የ “አይ ዲ 4 አፍሪካ” የዲጂታል መታወቂያ ለአፍሪካውያን ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚመክር ጉባዔ ነው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.