Fana: At a Speed of Life!

ተማሪ ደራርቱ ለሜሳን የገደለው ግለሰብ በ18 ዓመት እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረችውን ደራርቱ ለሜሳን በጩቤ ወግቶ የገደለው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣተወሰነበት፡፡

አቶ ዮሐንስ መርጋ ኢተቻ የተባለው ግለሰቡ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከጧቱ 2 ሰዓት 45 ሰዓት አካባቢ ጓደኛው የነበረቸውን ደራርቱ ለሜሳን በጩቤ ሶስት ጊዜ በመውጋት ህይወቷ እንዲያልፍ በማደረጉ የግድያ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡

በተደረገው ምርመራም ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ዐቃቤ ህግ የወንጀል ድርጊቱን የሚያስረዱ የሰው ማስረጃና የህክምና ማስረጃ በማስደገፍ ለሚመለከተው የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የክስ መዝገቡን መርምሮ ተከሳሹ የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 (1ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፉን አረጋግጧል።

በዚህም ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ በመሆኑ ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሹ ይታረማል፤ ማህበረሰቡንም ያስተምራል በማለት በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑን የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.