Fana: At a Speed of Life!

የግል ኦፐሬተሮች መደበኛ የመንገደኞችና የጭነት በረራ አገልግሎት እንዲያደርጉ ፈቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የግል ኦፐሬተሮች አሁን ከሚሰጡት የቻርተር በረራ በተጨማሪ መደበኛ የመንገደኞችና የጭነት በረራ አገልግሎት እንዲያደርጉ ፈቃድ ሰጠ፡፡

ባለሥልጣኑ ፈቃድ በመስጠቱ የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚገባውን አስተዋፅኦ ትርጉም ባለው ደረጃ ማበርከት እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ደህንነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ያበረታታል ብሏል።

አሁን ያሉት መደበኛ የሀገር ውስጥ በረራዎች ክልሎችን በዋናነት ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙ ሲሆኑ፥ ለግል ኦፐሬተሮች የተሰጠው ፈቃድ ክልሎችን ከክልሎች ለማስተሳሰርና የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተነግሯል።

በተጨማሪም በመንግስት ትኩረት ተሰጥቷቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎችን በቀላሉ ለጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

የዓየር ትራንስፖርቱን ለማሳለጥ ባለስልጣኑ የግል ባለሀብቶችን ጭምር በማሳተፍ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ21 በላይ የሚሆኑ ኤርስትሪፖችንና ሄሊፖዶች ለማስገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ከባለስከልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ለዓየር ትራንስፖርት ነባር አሰራሮችን በማዘመንና አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችንም መዘርጋቱ ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.