Fana: At a Speed of Life!

የአዘዞ-ጎንደር አስፓልት መንገድ ግንባታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በአዲስ ተቋራጭ የተጀመረው የአዘዞ -ጎንደር የአስፓልት መንገድ ግንባታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ እና የጎንደር ከተማ አመራር አባላት የአስፓልት መንገድ ሥራውን በዛሬው ዕለት ተመልክተዋል፡፡

የቢሮ ሃላፊው ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷የመንገድ ግንባታው ሳይጣናቀቅ ለዓመታት በመጓተቱ በህዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አመራር መሰረት የቀድሞውን ተቋራጭ ውል በማቋረጥ የመንገድ ግንባታው በአዲስ እንዲጀመር መደረጉን ገልፀዋል።

“አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ግንባታውን ተረክቦ በፍጥነት በማስጀመር እያካሄደ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪና የህዝቡንም የዓመታት ቅሬታ እንደሚፈታ ማረጋገጥ አስችሏል” ብለዋል ።

ዳግም የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ የሁሉንም አጋር አካላት ተሳትፎ በማጠናከርና ተቋማዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ምልከታውም በፍጥነት የተጀመረውን የአስፋልት መንገድ አሁናዊ ሁኔታ በመገምገም ተናጥላዊና የጋራ ሃላፊነቶችን መወጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አመራሩ በመስክ ምልከታው እንዳረጋገጠው 700 ሜትር የአስፋልት ማንጠፍ ስራን ጨምሮ በመንገዱ ግራና ቀኝ የድጋፍ ግንብና የአካፋይ መንገዶች ግንባታ ስራ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገንዘብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

”የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት መንገድ ስራ ለረጅም ዓመታት በመጓተቱ የህዝቡ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብሩክ አዳነ ናቸው፡፡

የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ቀሪውን ኪሎ ሜትር የመንገዱን አካል በፍጥነት ገንብቶ እንዲያጠናቅቅ ሃላፊነት እንደተሰጠው ጠቁመውል፡፡

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የአስፋልት ማንጠፍ ስራውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንየተደረገ መሆኑን ና ከ2 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የአፈር የድጋፍ ግንብ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት መንገድ ግንባታ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን÷ ግንባታው በ2010 በጀት ዓመት መጀመሩ ይሳወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.