Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።

የ27ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከግንቦት 22 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲካሄዱ የጨዋታ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ነበር።

ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ26ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በሚያደርጋቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በተያዘለት ጊዜ እንደማይካሄድ ማህበሩ ገልጿል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ መልስ በቀጣይ በሚገለጽ መርሐ ግብር ሊጉ እንደሚቀጥል ነው የተመላከተው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግንቦት 29 ከጊኒ ቢሳው፤ ሰኔ 2 ከጅቡቲ ጋር የማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለምድብ ጨዋታዎቹ ትናንት ለ26 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

45 ሀገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው በሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳውና ጅቡቲ ጋር ተደልድላለች።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን በምድቧ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በቡርኪናፋሶ 3 ለ 0 ስትሸነፍ ከሴራሊዮን ጋር ያለምንም ግብ አቻ ተለያይታ በ1 ነጥብ በምድቡ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.