Fana: At a Speed of Life!

ለመጠጥ ሒሳብ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት የከፈለው ግለሰብ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የገንዘብና የዶላር ኖቶችን ይዞ በመንቀሳቀስ በመዝናኛ ቦታ ላይ ለተጠቀመበት የመጠጥ ክፍያ ሀሰተኛ የገንዘብ ሲከፍል የተያዘው ግለሰብ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።

ደሳለኝ መብራቴ በተባለ ተከሳሽ ላይ በጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነው የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምስራቅ ሸዋ ዞን ዓቃቤ ሕግ ግለሰቡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 359 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት ክስ መስርቶበት ነበር።

በክስ ዝርዝሩ ላይ እንደተመላከተው ÷ተከሳሹ በኦሮሚያ ክልል መተሃራ ከተማ በመጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ መዝናኛ ቤት ውስጥ ለተጠቀመው መጠጥ ክፍያ ሀሰተኛ የብር ኖት ሲከፍል በአካባቢ የነበሩ የፀጥታ አካላት ባደረባቸው ጥርጣሬ መነሻ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ከዚያም በኋላ ባደረጉበት ፍተሻ 154 ሺህ የኢትዮጵያ ሀሰተኛ የብር ኖቶችና 2 ሺህ 300 ባለ 100 ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላሮችን ይዞ መገኘቱን በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረበበት ክስ ዝርዝር በችሎት ከደረሰውና በንባብ ከተሰማ በኋላ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸምና አለመፈጸሙን ለማረጋገጥ ፍርድ ቤተ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ ቃሉን ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ግለሰቡ በተከሰሰበት ድንጋጌ መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል፡፡

በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮ ተከሳሹን ያስተምራል በማለት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.