Fana: At a Speed of Life!

አቶ እንዳሻው በሆሳዕና የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሆሳዕና ከተማ እየተካሄዱ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው አሳሰቡ፡፡

በአቶ እንዳሻው ጣሰው የተመራ የክልል፣ የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አመራሮች ቡድን የከተማዋን የመንገድና ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል ።

በዚህ ወቅትም አቶ እንዳሻው ፥ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄዱ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ከተማው ስትራቴጂክና ብዙ የማደግ ተስፋና የመልማት አቅም እንዲሁም ትልቅ የንግድ ማዕከል መሆን እንደሚችል ጠቅሰው ፥ ከዚህ የበለጠ መልማት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የከተማውን ተስፋና አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል ያሉት አቶ እንዳሻው ፥ ለዚህ ስኬት ደግሞ የከተማው አመራር መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ሙስናን ማስወገድና ግልጽ አሰራር ማስፈን ይጠበቅበታል ብለዋል።

የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል ሲሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በተጨማሪም በክልሉ አሥር ማዕከላት በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የሚበቁ ዘመናዊ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች እንደሚገነቡ አንስተዋል፡፡

የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ እንዳሉት ፥ በከተማው በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ በ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ነው።
በተለይ 25 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታና በ260 ሚሊየን ብር ግንባታው እየተከናወነ ያለው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መጠቆማቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.