Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ -ሳዑዲ ግንኙነት መጠናከር ለቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል – አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ -ሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት መጠናከር ለቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ከሳዑዲ አረቢያ አቻቸው ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅት ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትፈልግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ ግንኙነታቸውን መሠረት በማድረግ በሰላም፣ በደህንነት፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ወቅቱ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በመተባበር በቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር የምታደርገውን ጥረት ሳዑዲ አረቢያ እንድትደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

በሳዑዲ አረቢያ በስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም አስረግድተዋል።

በሳዑዲ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አጋዥ ስለሆኑ የሀገሪሪቱ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ በበኩላቸው፤ የሀገራቱን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ስራ በሀገራቸው በኩል የሚደነቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

የግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር የሳዑዲ አረቢያ ፍላጎት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እያደረገች ያለውን አወንታዊ የሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ስራ በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልፀው፣ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በጋራ ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑና ለስኬታማነቱ መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.