Fana: At a Speed of Life!

ዩክሬን በሞስኮ የሙዚቃ ኮንሰርት አዳራሽ ጥቃት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጋለች ስትል ሩሲያ ወነጀለች

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ140 በላይ ሰዎች ለህልፈት በተዳረጉበት በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኝ ኮንሰርት አዳራሽ ላይ በተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው ሲሉ የሩሲያ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ አሌክሳንደር ቦርትኒኮቭ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ምርመራው መቀጠሉን ገልጸው፤ ነገር ግን ከወዲሁ የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ በዚህ ጥቃት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳለው መናገር ይቻላል ማለታቸው ተነግሯል።

የዓለም አቀፍ አሸባሪ ድርጅቶች ቅጥረኞች እና ታጣቂዎች ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከሰሜን አፍሪካ እና ከአፍጋኒስታን ወደ ዩክሬን እንዲሸጋገሩና የሩሲያን ጦር እንዲወጉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል ሲሉም የኔቶ ወታደራዊ ህብረትን ከሰዋል።

አይኤስ በፈረንጆቹ መጋቢት ወር ለተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነቱን እንደወሰደና የአሜሪካ ባለስልጣናትም ጥቃቱን የአፍጋኒስታን ቅርንጫፍ አይኤስ ኮራሳን መፈጸሙን የሚያሳይ መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሩሲያ ከጥቃቱ መፈጸም ጀርባ ዩክሬን እንዳለችበት ብትወቅስም፤ ዩክሬን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ምንም ግንኙነት እንደሌላት በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

አይኤስ ኮራሳን ጥቃት አድራሾቹን በማስተባበር ሚና እንደነበረው እና የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ቀጥተኛ ሚና እንደተጫወተ ቦርትኒኮቭ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.