Fana: At a Speed of Life!

ኃላፊነታችንን በመወጣት የሀገራችንን ሰላም እያፀናን እንቀጥላለን- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ፖሊስ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በቅንጅት በመወጣት የሀገራችንን ሰላም እያፀናን እንቀጥላለን ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

16ኛው የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባዔ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የክልልና የከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ተቋማት የየራሳቸውን ሰላምና ደኅንነት በማስከበር እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

እንደ ፖሊስም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በቅንጅት በመወጣት የሀገራችንን ሰላም እያፀናን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

ለፖሊስ ሥራ የጋራ የቴክኖሎጂ ዕድገት አስፈላጊ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ አቅሞች በአንዳንድ ክልሎች መጀመራቸውን ገልጸው÷ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች እንዲተገበሩ ማሳሰባቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

እንደ ሀገር አሁን ያለው የፀጥታ ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በጉባዔው የተመላከተ ሲሆን÷ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታየውን የጽንፈኞችና የሽብር ኃይሎች እንቅስቃሴ ለማክሸፍም ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊትና ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ተደርሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.