Fana: At a Speed of Life!

ሀገርን ውጥረት ውስጥ ለመክተት ሞክረው የነበሩ ሃይሎች ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ ደርሰዋል – ጄኔራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራችንን በተለያየ አቅጣጫ ውጥረት ውስጥ ለመክተት ሞክረው የነበሩ ሀይሎችን ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ ላይ አድርሰናል ሲሉ የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ከዕዙ የተለያዩ ክፍሎች በመመልመል በአመራር ትምህርት ቤቱ ያሰለጠናቸውን 2ኛ ዙር የበታች ሹም አመራሮችን አስመርቋል።

ጄኔራል አበባው ታደሰ በዚህ ወቅት፥ የሀገርን ዕድገት የማይፈልጉ ሃይሎች በራሳቸው ያቃታቸውን ፅንፈኞችን በማሰማራት ሀገርን ለመበታተን ቢሞክሩም በመከላከያ ሠራዊትና በህዝብ ድጋፍ ህልማቸው እንዲመክን መደረጉን ገልፀዋል።

ሀገራችንን ለማፅናት በተከፈለው ውድ ዋጋ የመጣውን ሰላም ለማረጋገጥም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ከየትኛውም የሀገሪቱ አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ተገንብቶ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡

ተመራቂ የበታች ሹም አመራሮች ያገኙትን አቅም በሚመደቡባቸው ቦታዎች በመተግበር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዝግጅቱ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ፣ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ፣ የደቡብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።

በዝግጅቱ ላይ ተመራቂዎች የተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶችን ማሳየታቸውን ከሠራዊቱ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.