Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ም/ቤት መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መደበኛ ሁለተኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ምክር ቤቱ በአንደኛ መደበኛ ስብሰባው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ትግበራ መገምገሙን አስታውቀዋል፡፡

በዲጂታል ምኅዳሩ የወጡ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ የአሠራር መመሪያዎችና ሌሎች ሠነዶች ከመንግሥት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገት ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸው በቀጣይ ተጠንቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል፡፡

ከስብሰባው በኋላም የአይ ሲ ቲ ፓርክ ልማትን መጎብኘታቸውን አቶ ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ ያሉበትን ውስን ተግዳሮቶች በመፍታት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና ከመንግሥት ጋር ያለውን መደጋገፍም የሚያጠናክር ቁመና እንዲላበስ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷ ብለዋል፡፡

በአይ ሲ ቲ ፓርክ ውስጥ በዳታ ሴንተር ዘርፍ የተሰማሩ ሁለት ድርጅቶችንና የኢንኩቤሽን ማዕከልን መጎብኘታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቶቹ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት አስፈላጊውን መሰረተ-ልማት አሟልተው ዝግጅት ከማጠናቀቃቸውም በላይ ለደንበኞቻቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተመልክተናል ነው ያሉት።

በአጠቃላይ በፓርኩ ያዩት የሥራ እንቅስቃሴ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ ትልቅ ተቋም እየተገነባ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.